ኃይለሥላሴ በጥበባቸው የተደነቁባቸው ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር በአንድ ሜዳ የተጫወቱት የጥበብ ሰው፡፡

0
173

ጥበብ የአፋቸው መፍቻ፣ የስሜታቸው መግለጫ የታሪካቸው ትልቁ ክፍል ነው፡፡ በወርቃማው የጥበብ ትውልድ ውስጥ ወርቅ የሆነ ሙያቸውን ለሕዝብ አድርሰዋል፡፡ ለጥበብ ከነበራቸው ትልቅ ፍቅር የተነሳ በ15 ዓመታቸው ወታደር ሆነዋል፤ ታላቁ የጥበብ ሰው፡፡ ብዙዎች የት ደርሰው ይሆን? ብለው ጠይቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በዚያ ዘመን የተጫወቷቸውን ዜማዎች እያዳመጡ በትዝታ ያስቧቸዋል፡፡ እኔም ብሆን በዚያ ዘመን የዘፈኗቸውን ዘፈኖች እያምሰለሰልኩ ከመኖር ውጭ የት እንደሚኖሩ አላውቅም ነበር፤ አሁን ግን ዕድል ገጥሞኝ ከአሰብኩት በታች በመጻሕፍት፣ በሲዲ፣ በድምጽ ማጉያና እድሜያቸው ቆዬት ባሉ ካሴቶች በተከበበች ትንሽዬ ‹ሚኒ ሚዲያ› ውስጥ እየሠሩ አግኝቻቸዋለሁ፤ ታሪካቸውን በአጭሪ አብረን እንቃኝ፡፡
እኒህ ሰው ከያኒ ዓባይነህ ደጀኔ ናቸው፡፡ የተወለዱት በግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1940ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ ዓባይነህ ዓለም አልጋ በአልጋ ሆና አልተቀበለቻቸውም፡፡ በእናት እቅፍ ሞቀው፣ በጉያዋ ቦርቀው ማደግ አልታደሉም፡፡ ይልቁንስ በተወለዱ በሦስት ወራቸው ወላጅ እናታቸውን በሞት ተነጠቁ፡፡ ጊዜው ነብስ ላለወቁት እንቦቅልላ ጨቅላ ፈተናቸውን የጀመሩበት ነበር፡፡ አባታቸው 10 አለቃ ደጀኔ የንጉሡ ወታደር ስለነበሩና ለሥራ ሌላ ቦታ ስለነበሩ የልጃቸው እናት ስትሞት ቀብር ላይ አልነበሩም፡፡ ከቀብር በኋላ ሊደርሱ ወደሻሸመኔ ይሄዳሉ፡፡ ያኔ ነብስ ያለወቁ ልጃቸውን ባዩ ጊዜ አብዝተው አዘኑ፡፡ ተጨነቁም፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ ምንም ማድረግ ስላልቻሉ ልጃቸውን ከአያታቸው ጋር ጥለው ተመለሱ፡፡ በዚህ አልቀሩም ትንሹ ብላቴና አንድ ዓመት ከስምንት ወር ሲሆነው ከአያታቸው አሾልከው ወደአዲስ አበባ ይዘውት ኮበለሉ፡፡
10 አለቃ ደጀኔ በደንብ አፍ ያልፈቱ ልጃቸውን ይዘው በአራተኛ ክፍለ ጦር ተቀመጡ፡፡ ልጃቸውን ታሳድግ ዘንድ ሌላ ሚስትም አገቡ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በአንድ ሚስት መጽናት አልቻሉም፡፡ ልጃቸውን ያለ እንግልት ባይታዋርነት ሳይሰማቸው እንዲያሳድጉላቸው የሚያገቧቸው ሴቶች ሁሉ ለልጃቸው የተመቹ አልነበሩምና ለልጃቸው ምቾት ሲሉ ብቻ 13 ያክል ሴቶችን እንዲያገቡ ተገደዱ፡፡ ብላቴናው ዓባይነህ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በአዲስ አበባ የቄስ ትምህርት ቤት ገባ፡፡
በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሮ ማንበብና መጻፍ ሲችሉ ሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት በመግባት መደበኛ ትምህርታት ጀመረ፡፡ ታናሹ ልጅ የብዕር አጣጣሉ፣ የቀለም አቀባበሉና ያለው ተሰጥኦ ከአንደኛ ክፍል ከፍ ያለ ስለነበር የነበረውን ፈተና አልፎ ሦስተኛ ክፍል ገባ፡፡ በልጅነቱ ጀምሮ በየመንገዱ፣ በየሠርግ ቤቱና በተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ ያንጎራጉርም ነበር፡፡ ብዙዎችም በልጅነት እድሜው በነበረው ተሰጥዖ ይደነቁበት ነበር፡፡
አባታቸው 10 አለቃ ደጀኔ ለሰንደቅ ዓላማ የተዋደቁ በየጦር ግንባሩ የዘመቱ ጀግና ቢሆኑም ትምህርት አልነበራቸውም፡፡ አንድ መልካም ጓደኛቸው ስማቸውን እንዲጽፉና ቁጥር እንዲያውቁ እስኪያስተምራቸው ድረስ ለረጅም ዓመታት በዱካ ነበር የፈረሙት፡፡ የትምህርት ደረጃን የሚለኩትም በቁጥሩ ከፍተኛነት ነበር፤ በእርሳቸው አረዳድ አንደኛ ደረጃ ከሚወጣ ተማሪ አስረኛ ደረጃ የሚወጣው የተሻለ ጎበዝ ነው፡ የልጃቸው የትምህርት ደረጃም እርሳቸው ከሚገምቱት 100 የበለጠ እንዲሆን የዘወትር ምኞታቸው ነበር፡፡ እንዲያው ከ50 እና 60 ደረጃ ያነሰ ልጃቸው ካስመዘገበማ ማበዳቸው ነው፡፡
ከያኒ ዓባይነህ ከአንደኛ ወደ ሦስተኛ ክፍል ‹በተርም› ካለፉ በኋላ የነበረውን ገጠመኝ እንዲህ ነበር ያስታወሱት፤ ‹‹ሦስተኛ ክፍል ስገባ ተማሪዎቹ 52 ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቅቆ በሁለተኛው አጋማሽ ነበር የገባሁ፡፡ ከእነሱ ጋር የማጠቃለያ ፈተና ተፈትኜ የመጨረሻ ደረጃ ሲነገር 49ኛ ደረጃ ወጣሁ፡፡ ይህን ደረጃዬን ይዤ ወደቤት ስሄድ አባቴ አየውና ደስታው እጥፍ ድርብ ሆነ፡፡ ወደመርካቶ ይዞኝ ሄደ፡፡ ሙሉ ልብስ እስከነጫማው ገዛልኝ፡፡ ከልብስ ቤቱ እንደወጣን የደስታችን ቀን ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ወደፎቶ ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ ፎቶ ተነስተን ወደ ስጋቤት ሄድን፡፡ በስጋ ቤትም ከሽንጡም ከወርቹም ከሁሉም ዓይነት አስቆርጠን ወደቤት ሄድን፡፡ ቡናው ተፈላ፤ ወጡ ተሠራ፤ ጎረቤት ተጠራ፤ የእኔ ደረጃ ለጎረቤት እየተነገረ ደስታ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ስኬታማ እንድሆን ተምርቄ ተለያዬን›› ብለውኛል፡፡
ብዙ ስለትምህርት ደረጃ ያላወቁት 10 አለቃ ደጀኔ ልጃቸው 49ኛ ስለወጣ ደስታቸው ከልክ አልፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመርቀው እንደሚያሳልፉላቸው በመተማመን የተለዬ እንክብካቤ ያደርጉላቸው ጀመር፡፡ ጎረቤቶቹ ግን ግር ሳይሰኙ አልቀሩም፡፡ ታላቅ ተስፋ የተጣለባቸው ዓባይነህም ጠንክረው በማጥናት በዓመቱ ከ52 ተማሪ 1ኛ ወጥተው ተሸለሙ፡፡ ደስታቸውን ለዓባታቸው እስኪናገሩም ተቻኩለው ነበር፤ ደስታቸውን በደስታ የሚቀበል ግን አላገኙም፡፡ ዓባይነህ ያን ቀን ሲያስታውሱት ‹‹1ኛ ወጥቼ የምስክር ወረቀት ተቀብዬ መጣሁ፡፡ አባቴ መጠጥ ይወድ ነበርና መጠጥ ከሚጠጣባት ቤት እያለ የጎረቤት ልጆች የትምህርት ካርዳቸውን ይዘው እንደተመሱ ሲሰማ የእኔን ደረጃ ሊያይ የሚጠጣውን ሳይጨርስ ሲከንፍ መጣ፡፡ እንደደረሰ ‹እንዴት ነህ ጎረምሳው? ወረቀት አላመጣህም?› አለኝ፤ እረ አምጥቻለሁ አባዬ አልት፡፡ ‹ጎሽ በል አምጣና አሳዬኝ?› ወስጄ አቀበልኩ፤ ወረቀቷን በድንብ ተመለከታት የሚጠብቀው ቁጥር አልነበረም፡፡ ‹ምንድን ነው ይህ ቁጥር›? አንደኛ ወጥቼ ነው አባዬ፤ ‹አንድ ቁጥር?!› አዎ! አንደኛ! ‹ወይኔ 10 አለቃ ደጀኔ የማንም ልቅምቃሚ ትክሻው ላይ ኮኮብ እያደረገ ሲገላምጠኝ እየዋለ! አንተ ተምረህ ታሳልፍልኛለህ ስል የመጨረሻ አንድ ቁጥር ታመጣለህ?!› ወረቀቱን ከላዬ ላይ ጥሎብኝ ወጥቶ ሄደ›› ብለዋል፡፡
ድግሱ ካለፈው ዓመት በልጦ እሸለማለሁ ብለው ሲያስቡ የነበሩት ዓባይነህ ነገሩ ዱብ ዕዳ ሆነባቸው፡፡ በሽልማት ፋንታ ከአባታቸው የሚመጣውን ቅጣት መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ 10 አለቃ ደጀኔም የ4ኛ ክፍለ ጦር ቤቶች ተዘጋግተው ሰው ሁሉ እስኪተኛ ድረስ ከቆዩ በኋላ መጠጥ በተጨማመረበት የቁጣ ኃይል ተመለሱ፡፡ ቀጥታ ወደቤት አልገቡም ሁሉንም ቤቶች በውጭ በኩል ዘግተው ወደቤታቸው ገቡ፡፡ ከዚያም በእርሳቸው አስተሳሰብ 1ኛ ወጥቶ ያሳፈራቸውን ልጃቸውን በሸራ ቀበቶ ይመሸልቋቸው ጀመር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ባለቤታቸው ለመገላገል ቢሞክሩም እርሳቸውም ቀመሱ፡፡ ሰፈሩ በእሪታ ቀለጠ፡፡ በየቤቱ የተኛው ወታደር ሁሉ ከቤት ለመውጣት ሲሯሯጥ ቤቱ በሙሉ በውጭ በኩል ተዘግቷል፡፡ ደግነቱ የቤታቸው ጣሪያ ቀዳዳ መሆን ዓባይነህን አተረፋቸው፡፡
ከእነርሱ ቤት አጠገብ ይኖር የነበረ አንድ በቅርብ ከግዳጅ የተመለሰ ወታደር በቤታቸው ጣሪያ ባለው ክፍተት ሾልኮ በመግባት ሕይወታቸውን ታደገው፡፡ 10አለቃ ደጀኔ ቤተሰቡን ለምን እንደሚገርፉ ሲጠየቁም የሆነውን ሁሉ አስረዱ፡፡ ወታደሩ ሁሉም በነገሩ ተገርሞ የሆነውን ሁሉ ቤት ለተዘጋባቸው ሌሎች ወታደሮች እየከፈተ ተነገረ፡፡ ጎረቤቱ ሁሉ በ10 አለቃ ደጀኔ ተሳሳቀ፤ እርሳቸውም ጉዳዩን ሲያውቁ ተጸጸቱ፡፡ ግርፋቱ መሆን ቢኖርበት እንኳን 49ኛ ደረጃ የወጡ ጊዜ ነበር፤ ልጃቸውንም በቅባት ያሹ ጀመር፡፡ ይቅርታ እንዲያደርጉላቸውም ተማጸኗቸው፡፡
እኒህ ፈተና የተደራረበባቸው ከያኒ በየደረሱበት ከማንጎራጎር የሚያስቆማቸው ግን አልነበረም፤ ትምህርታቸውንም ቀጠሉ፡፡ በ1955ዓ.ም እርሳቸው የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ማለት ነው የክቡር ዘበኛ ወጣት የሙዚቃ ቡድን ልጆችን በሙዚቃ ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ከልጅነት ጀምረው ሙዚቃ የልብ ምታቸው የሆነው እኒህ ሰው የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድንን ለመቀላቀል ተመዘገቡ፤ የተሰጠውን ፈተናም በብቃት አለፉ፡፡
አባታቸው 10 አለቃ ደጀኔ የክቡር ዘበኛ መመዝገባቸውን ሲያውቁ ‹‹በፍጹም አይሆንም›› አሉ፡፡ በእርግጥ 10 አለቃ ደጀኔ አይፈረድባቸውም፤ ለደስታቸው ሲሉ 13 ሚስቶችን አግብተው ተስፋ የጣሉባቸው የልብ ልጃቸው ናቸውና፡፡ አይሆኑም ይበሉ እንጂ ዓባይነህን ማስቀረት ግን አልቻሉም፡፡ ብላቴናው በ15 ዓመታቸው የልጅነት ወታደርን ተቀላቅለው ደብረ ብርሃን ማሰልጠኛ ገቡ፡፡ በዚህ የተጀመረው የውትድርና እና የሙዚቃ ሕይወታቸው በወታደር ቤት ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ሙዚቃውንም ውትድርናውንም በደንብ አወቁት፡፡ በድምጻቸው ያቀነቅናሉ፣ ቫዮሊን ይጫወታሉ፣ ይወዛወዛሉ ውዝዋዜም ያሰለጥናሉ፡፡ የከፋ ቀን ሲመጣም ወታደር ናቸውና ይዋጋሉ፡፡
በወታደር ቤት ቆይታቸው ከጃንሆይ ጋር የመገናኘት እድል አገኙ፡፡ በቤተ መንግሥት የሌሎች ሀገራት መሪዎችና ነገሥታት ሲመጡ የሙዚቃ ቡድኑ ይጠራ ነበርና ከጃንሆይ ፊት መጫወት ጀመሩ፡፡ በተለይም በቫዮሊን አጨዋወታቸው የጃንሆይን ቀልብም መሳብ ቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የገጠማቸውን ገጠመኝም አጫውተውኛል፡፡ ‹‹በሀገር ፍቅር ቫዮሊን እየተለማመድን እያለ ጃንሆይ ለጉብኝት እንደሚመጡ ተነገረን፡፡ ‹ሥራችሁን ሳታቋርጡ ሥሩ› ተባልን፡፡ የተባለው አልቀረም ጃንሆይ መጡ፡፡ እርሳቸው ወደ ቤት ከመግባታቸው በፊት ነጯ ውሻቸው ቀድማ ትገባለች፡፡ ውሸዋ እኛ ወዳለንበት ዘልቃ የምጫወትበትን መሣሪያ እየነካካች በእግሬ ስር ስትገባ ዞር በይ ብዬ በእግሬ ገፋ አደረኳት፡፡ ልሙትልህ ጠባቂያቸው ከየት መጣ ሳልለው ‹ምን አባህ ሆንክ አንተ? ነካሃትስ?!› አለኝ፡፡ እረ ጌታዬ መሳሪያዬን ነክታብኝ ነው ብዬ ዝም አልኩ፡፡ የተከበረች መሆኗን አላውቅም፡፡ በኋላ ጓደኞቼ ከሞት እንደተረፍኩ ሲነግሩኝ ገረመኝ›› ብለውኛል በትዝታ መነጽራቻ ድረዋቸውን ሲነግሩኝ፡፡
ዓባይነህ በኋላም የ7 ዓመታት የውትድርና ግዳጃቸውን አጠናቅቀው ለመውጣት ሲጠይቁ ለጓደኞቻቸው ሲፈቀድ እርሳቸውን የሚተካ ባለሙያ ለቤተ መንግሥት ስላልነበር ፈቃዱን ተከለከሉ፡፡ እርሳቸው ግን በዚያው መቆዬቱ አልፈለጉትም፡፡ ከውትድርናው ዓለም ወጥተው በሙዚቃ ሙያቸው ማበብ ነበር ፍላጎታቸው፡፡
በ1964ዓ.ም ‹‹የወይን እሸት እሸቴ፣ የበረሐ ሎሚ፣ ባልንጀሬ፣ እዮብ እዮቤን›› እና ሌሎችን ተጫወቱ፡፤ በተለይም የወይን እሸት እሸቴ፣ የበረሐ ሎሚ እና ባልንጀሬን በሸክላ አስቀርጸው በብዙ ሰዎች ልብ ቀርተዋል፡፡ ከያኒ ዓባይነህ ከውትድርናው እንዳይወጡ ከቤተ መንግሥትም እንዳይጠፉ ስለተፈለገ ፈቃድ ሲከለከሉ ለመውጣት የተጠቀሙትን አማራጭ እንዲህ ነበር የነገሩኝ፡፡ ‹‹እንደማይፈቀድልኝ ሳውቅ አበድኩ ብዬ ጮሁኩ፣ ከዚያም አማኑኤል አስገቡኝ፡፡ ዶክተሩ ‹ምን ሆነህ መጣህ?› ሲለኝ አበደ ብለው አይደል ያመጡኝ አልኩት፡፡ ከዚያም ሊመረምረኝ ጎኔን ሲነካኝ ፎክሬ መታሁት፡፡ ‹እውነትም አብዷል› ብሎ ጻፈብኝ፣ እኔም ወጣሁ›› በሕመም ሰበብ ከውትድርናው የወጡት ዓባይነህ ጊዜ ሳይፈጁ ሀገር ፍቅር ቲያትር ገቡ፡፡
በሀገር ፍቅር በቆዩበት ጥቂት ጊዜ ተወዳጅነታቸው ላቅ እያለ ሄደ፡፡ እርሳቸውም በምሽት ቤቶችና በተለያዩ የባሕል አዳራሾች እየተዘዋወሩ የሙዚቃ ጥማቸውን ይወጡ ጀመር፡፡ በሀገር ፍቅር ቲያትርም ለስምንት ወራት ያክል እንደቆዩ በወቅቱ ሐረር ይኖር የነበረው ሦስተኛ ክፍለ ጦር የውዝወዜ አሰልጣኝ፣ የሙዚቃ ተጫዋችና ድምጻዊ ሰው እንደሚፈልግ ተሰማ፡፡ ከዓባይነህ ቀደም ብለው ታላቁ አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ሰምተው ስለነበር ዓባይነህን ወደዚያ እንዲሄዱ ጠየቁት፡፡ ንን ቦታ የሚመጥኑ ዓባይነህ እንደሆኑ አውቀው ነበርና፡፡ እርሳቸውም ከሀገር ፍቅር ወጥተው ወደ ሀረር አቀኑ፡፡
በሀረር ሦስተኛ ክፍለ ጦር ድምጻዊና የውዝዋዜ አሰልጣኝ ሆነው ማገልገል ጀመሩ፡፡ እስከ 1970ዓ.ም በዚያው ቆዩ፡፡ በሀረር ቆይታቸው ሚስት አግብተው ልጅ ወልደዋል፡፡ በዚሁ ቆይታቸው ከሌትናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር በአንድ ሜዳ እግር ኳስ እስከመጫወት ደርሰዋል፡፡ ዓባይነህ በሦስተኛ ክፍለ ጦር የሙዚቃ ቡድኑን ወክለው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ደግሞ በዚሁ ክፍለ ጦር መሳሪያ ግምጃን ወክለው ኳስ ይጫወቱ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የጃንሆይ ዘመን ተጠናቅቆ ደርግ ስልጣን ሲቆጣጠር ስርዓቶችም አብረው ተቀየሩ፡፡ ከጥበብ ውጭ ፖለቲካ ጋር ንክኪ የሌላቸው ከያኒው በ1971ዓ.ም የፖለቲካ እስረኛ ተብለው ከርቸሌ ገቡ፡፡ ያለምንም ፍርድ ለአራት ዓመታትም በእስር ቤት ማቀቁ፡፡ ግን በዚያ ውስጥ ሆነውም ከዘፈን ያስቆማቸው አልነበረም፡፡
ወደ እስር የገቡበት ወቅት ባለቤታቸውን በሞት ተነጥቀው እንባቸው ሳይደርቅ ጥቁር ሳያወልቁ ነበር፡፡ ሐዘናቸውን የሚያስረሳ በሚፈልጉበት ወቅት ይባስ ብለው ወኅኒ ወረዱ፡፡ ያለ ፍርድ የአራት ዓመታትን እስር ጨርሰው እንደወጡ ሚኒሻ ሠራዊትን ተቀላቅለው ድሬደዋ ተቀመጡ፡፡ በዚያውም ከ9ኛ ክፍለ ጦር ጋር የሙዚቃ ሥራዎችን ይሠሩ ጀመር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሙዚቃ ሥራ ይሠሩበት የነበረው ክፍለ ጦር የቦታ ለውጥ አድርጎ ወደሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በመምጣት ሽሬ ተቀመጠ፤ የሙዚቃ ክፍሉ ግን ከዚያው ቀረ፡፡ 9ኛ ክፍለ ጦር ሽሬ ላይ ዓመታዊ ክብረ በዓሉን ሊያከበር የቀድሞ ሙዚቃ ቡድኖቹ እንዲመጡላቸው ጥሪ አቀረበ፤ እነ ዓባይነህም ጉዟቸውን ወደሽሬ ጀመሩ፡፡
ጓዛቸውን ሸክፈው መቀሌ ሲደርሱ ነገሩ ሁሉ ተበላሽቶ የደርግ ወታደር እየሸሸ ነበርና መቀሌ ላይ እንዲመለሱ ተደረጉ፡፡ በመቀሌ የጦር መሣሪያቸውንና የሙዚቃ መሣሪያቸውን አስረክበው ተመለሱ፡፡ ያ ብቻ አይደለም እንዲበተኑም ተደረገ፡፡ በዚህ ሲያዝኑ በ1984ዓ.ም በአዲሱ መንግሥት ሰልጥነው መታወቂያ ከሌላቸው መኖር አይችሉም የሚል ትዕዛዝ ተላለፈባቸው፡፡ ከያኒው ኑሯቸው አልጋ በአልጋ አይሁን ሲላቸው ደዴሳ ማሰልጠኛ ገብተው ለ8 ወራት ያክል አዲስ ወታደራዊ ስልጠና ሰለጠኑ፡፡
በዚህ ችግር ውስጥ ሆነውም መዝፈን አላቆሙም ነበር፡፡ ከማሰልጠኛው ሲወጡም ስለኤች አይቪ ኤድስ፣ ስለሀገር እንድነት፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወታደሩን የሚያነቃቃና ሌሎች ዘፈኖችን ዘፍነዋል፡፡ አዲስ አበባ ኑሯቸውን አድርገው ሳለ በጄኔራል ገብረጊዮርጊስ አማካኝነት ኮምቦልቻ ሰፍሮ ከነበረው ጦር ጋር ቀላቀለቀቸው፡፡ የነበራቸው ሙያም ሙዚቀኝነት ነበር፡፡ እኒህ ልጅ ጀምረው ሙዚቃን የሚወዱት ታላቅ ሰው ከእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ተዘራ ኃይሌ፣ መንበረ በዬና እና ሌሎቹም ጋር በአንድ መድረክ ሲዘፍኑ ነበር የቆዩት፡፡
ኮምቦልቻ ከመጡ በኋላ የሙዚቃ ሕይወታቸው እየደከመ መጣ፡፡ በሚፈለጉት ልክ የሚያሠራቸውና ጥበባቸውን የሚያግዛቸው ሲያጡ ኑሯቸውን ለመምራት ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በቧንቡ ውኃ ሥራና ሌሎችም ሥራዎች መተዳደር ጀመሩ፤ በዚያውም ቆዩ፡፡ ብዙዎች እነ መሀሙድ አህመድ እና እነ ጥላሁን ገሰሰ በሄዱበት መንገድ ይሄዳሉ ብለው ሲጠብቋቸው የሥርዓት መፈራራቅና አጋዥ ማጣት ከነበሩበት አውርዶ ሕይወታቸው በአንዲት ሚኒ ሚዲያ ውስጥ እንዲወሰኑ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን ላይ በኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ሚኒ ሚዲያ ውስጥ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ከያኒ አባይነህ በሙዚቃው ባተረፉት መልካም ስም በርካታ የመስክር ወረቀቶች ከተለያዩ አካላት ተበርክቶላቸዋል፡፡ አሁን ላይ በኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ሠራተኛ ከሆኑ ሴት ጋር ትዳር መስርተው እየኖሩ ነው፡፡ በባለቤታቸው መልካምነትና በሀገሩ ደግነት ከኮምቦልቻ ወጥተው ለመኖር እንደሚጨንቃቸው የሚናገሩት ዓባይነህ ከውድ አብረዋቸው ካሉት ባለቤታቸው ልጅ ባለማግኘታቸው ደስታቸው ሙሉ አይደለም፤ ነገር ግን ከሌላ የወለዷቸው አምስት ልጆች አሏቸው፡፡ ከያኒው በሙዚቃ መሣሪያ ችሎታቸውና ድምጻቸውን አይቶ የሚያሠራቸው ሰው ቢያገኙ አሁንም ከመሥራት ዓይናቸውን እንደማያሹ ነግረውኛል፡፡
‹‹እኔ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊነቴን በፍጹም ለድርድር አላቀርበውም፡፡ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩና ኢትዮጵያዊነቴን ስለማከበር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ኖሬያለሁ፤ አሁንም እኖራለለሁ፡፡ ምላሴን ቢቆርጡት ስለኢትዮጵያዊነት መልካም ከመናገር አላቆምም፤ ማንም ይምጣ ማንም ይግዛ ከኢትዮጵያ ምድር እስካልወጣ ድረስ ተቃውሞ የለኝም፡፡ ክፉ ቢሰራ እንኳን ኢትዮጵያዊነቴን አይሸረሽረውም›› ዓባይነህ ስለኢትዮጵያዊነት ሲናገሩ፡፡
በዜማቸው እያዜማችሁ፣ እየተደሰታችሁና በትዝታቸው ስትባዝኑ የነበራችሁ የዘርፉ ባለሙያዎች ከያኒው ሙያቸውን እንዲያወጡ ብታደርጓቸው እንላለን፡፡ ለአሁኑ ቋጨሁ፤ ሠላምም ተመኘሁ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here