“አማራ ክልልን እንደሚወራው ሳይሆን በተቃራኒው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡” የተማሪ ወላጆች

0
58

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውክ ምንም ዓይነት የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት መደረጉን ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ዛሬ ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም መቀበል ጀምሯል፡፡ ነባር ተማሪዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ አዲስ ተማሪዎችን በጥሩ መስተንግዶ ሲቀበሉ አብመድ ቦታው ድረስ ተገኝቶ ተመልክቷል። የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር በማሰብ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን መድቦ ከጎንደር ከተማ ጀምሮ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው፡፡

ተማሪዎች እና ወላጆችም በተደረገላቸው መልካም አቀባበል ደስተኞች እንደሆኑ አስተያዬታቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ከጉራጌ ዞን ቡታጅራ ነው ልጃቸውን እና የሌሎች ተማሪዎችን ወላጅ ወክለው ተማሪዎችን ለመሸኘት የመጡት አቶ ሰለሞን ጥበቡ የተማሪዎችን እንግልት ለመቀነስ እየሰራው ላለው ተግባር ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል።

የትግራይ ክልል ተማሪዎችን በአማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለመላክ እንደማይፈልግ መግለጹን ተከትሎ ስጋት ውስጥ ገብተው እንደነበር የተናገሩት አቶ ሰለሞን “አማራ ክልልን እንደሚወራው ሳይሆን በተቃራኒው ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል፡፡ ጎንደር ከተማ ሲገቡ ጀምሮ የተደረገላቸው አቀባበል ሰላም እና እፎይታ እንዲሰማቸው ማድረጉን፣ ስለ ክልሉም ሆነ ስለ ጎንደር የሚወራውም የፈጠራ ወሬ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከተለያዩ ክልሎች ተነስተው ተማሪዎችን ለመሸኘት ደባርቅ የተገኙ እና አብመድ ያነጋገራቸው ሌሎች ወላጆችም የአቶ ሰለሞንን ሀሳብ ተጋርተዋል፡፡

ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን ሰላም አስጠብቀው፣ ህግና ደንብ አክብረው እና የወላጆቻቸውን ምክር ተቀብለው በሰላም እንዲማሩም መልዕክት አስተላልፈዋል። የዩንቨርሲቲውን ሰላም በባለቤትነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም ተማሪዎች አረጋግጠዋል።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት እየሩስ በሪሁን ተማሪዎችን እስከ ጎንደር ከተማ በመሄድ ለመቀበል ቀደም ብሎ በተደረገው ዝግጅት መሠረት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ነግራናለች፡፡ በተያዘው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውክ ምንም ዓይነት የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቃለች፡፡

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ከጀመረ ሦስተኛ ዓመት ሆኖታል፡፡ በመሆኑም በትምህርት ዘመኑ ማጠናቀቂያ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያስመርቅ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከደባርቅ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here