አርሰናል በብራይተን ተሸነፈ፤ የኤቨርተኑ አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫም ተሰናበቱ፡፡

0
65

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 15ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ትናንት በሜዳው ብራይተንን የገጠመው አርሰናል 2ለ1 ተሸንፏል፡፡ ዋና አሰልጣኙን አሰናብቶ በጊዜያዊ አሰልጣኝ በሜዳው የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አርሰናል በብራይን ሆቭ አልብዮን መመራት የጀመረው ገና በ36ኛው ደቂቃ ዌብስተር ባስቆጠራት ግብ ነበር፡፡

ከእርፍት መልስ ለ100ኛ ጊዜ ለመድፈኞቹ የተሰለፈው ላካዜት በ50ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ መልሶት ነበር፡፡ ነገር ግን በ80ኛው ደቂቃ ማውፔይ ለብራይን ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ የመድፈኞቹን ሽንፈት አስቀጥሎታል፤ አርሰናል ባለፉት ባደረጋቸው የፕሪሚየር ሊግና ሌሎችም ውድድሮች ዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል በደረጃ ሠንጠረዡ 10ኛ ላይ ሲቀመጥ ብራይተን ከወራጅ ቀጠናው ወጥቶ ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በ18 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ሆኗል፡፡

ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ኤቨርተን አሰልጣኙን በማሰናበት አርሰናልን ተከትሏል፡፡ ላለፉት 18 ወራት ኤቨርተንን የመሩት አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ ከመርሲሳይዱ ደርቢ የ5ለ2 ሽንፈት ማግስት መሠናበታቸው ይፋ ሆኗል፡፡

በሊቨርፑል 5ለ2 በአንፊልድ የተሸነፉት ማርኮ ሲልቫ በ9ኛ ሽንፈታቸው ቡድኑን በሊጉ ወራጅ ቀጠና 18ኛ ላይ በማስቀመጣቸው ስንብታቸው ፈጥኗል፡፡ ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ 60 ጨዋታዎችን ያደረጉት አሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ በ24 ጨዋታዎች አሸንፈው በ24 ጨዋታ ተሸንፈዋል፤ በ12 ደግሞ አቻ ተለያይዋል፡፡

ኤቨርተን በቀድሞው አጥቂው ዱንካን ፈርጉሰን ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ነገ ቸልሲን ይገጥማል፡፡ በሊጉ የስንብት ድባብ ያዣበባቸው ሌላኛው አሰልጣኝ ኦሊጎናር ሶልሻዬር ከትናንት በስቲያ ማሸነፋቸው ያረጋጋቸው ቢመስልም ቆይታቸው አስተማማኝ አይደለም፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here