ኢትዮጵያውያን እስከነባህላቸውና ወጋቸው ደብረማርቆስ ላይ እየተሰባሰቡ ነው፡፡

0
72

በኢትዮጵያውያን የሚከወኑ ባህሎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት አገራዊ የባህል ስፖርት ውድድር በአማራ ክልል ይደረጋል፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያውያንን እስከነባህላቸውና ወጋቸው በማገናኜት አንዱ የሌላኛውን ባህል እንዲያውቅ በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን እያሳዩ ይኖሩበታል፡፡ ከውድድሩ ባለፈ በተወዳደሪዎች የሚታዬው ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡

ይህ በጉጉት የሚጠበቀው አገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር በአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ይካሄዳል፡፡ የውድደሩን ዝግጅት በተመለከተ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳት ዓለም ሁነኛው ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ አስጀምሮ ለማስፈጸም ፌዴሬሽኑ ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞንና ከደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

17ኛው አገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 13ኛው የባህል ፌስቲቫል ከየካቲት 7 – 15 ቀናት 2012ዓ.ም ድረስ በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ይደረጋል፡፡ የአማራ ክልል የዘንድሮውን ጨምሮ ለሦስተኛ ጊዜ ሲያስተናግድ ከዚህ በፊት ያስተናገዳቸውን ውድደሮች በጥሩ ሁኔታ ማዘጋጀቱን ፕሬዝዳቱ ተናግረዋል፡፡ የዘንድሮውን ውድድርም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ለማዘጋጀት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በ17ኛው የባህል ስፖርቶችና 13ኛው የባህል ፌስቲባል የሚሳተፉ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች መግባት ጀምረዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተወሰኑ ክልሎች ልዑካን ገብተዋል፤ ቀሪዎች ክልሎችም ዛሬ እንደሚገቡ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የሀረሪ ክልል መሳተፍ እንደማይችል ለኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በማሳወቅ በውድደሩ እንደማይሳተፍም ታውቋል፡፡ ውድድሩ በ11 የውድደር ዓይቶች ይደረጋል፡፡ የአማራ ክልል በሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች በሁሉም ውድድሮች ሙሉ ተወዳደሪዎችን በመያዝ በመሳተፍ እንደሚታወቅ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ እስከዛሬ በተደረጉ ውድድሮች 10 ጊዜ በማሸነፍ ቀደሚ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here