“ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ሙስሊም፣ መስጅድ ሲሠራ ክርስቲያን የአሰሪ ኮሚቴ አባል የሚሆኑባት ሀገር ናት፡፡” የሃይማኖት አባቶች

0
47
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) “ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው” እንዲሉ ሰውን ሰው ሲገድለው የሚቀብረው ሰው ነው፡፡ ሰው ሰውን ሲያቆስለው ሕክምና የሚሰጠው ሰው ነው፡፡ ነገሥታት ሰውን ፈርተው አጃቢና አጋፋሪ ሰው ይቀጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰው ተፈሪም አስፈሪም ገዳይም አዳኝም ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታሪክ እንደምንረዳውም አባቶች እንደሚነግሩንም በወዳጃቸው ላይ ክንዳቸውን አያነሱም፤ ጦር አይሰብቁም፡፡ በፍቅር፣ በሠላም፣ በአንድነትና በጽናት ያምናሉ፡፡ ነገር ግን አንድነታቸውን የሚፈታተን ቢኖር ወንዝ ሳያሻግሩ፣ አንበርክከው ሳያስገብሩ አይመለሱም፤ ለዚህ ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አማኞች ናቸው፤ በፈጣሪያቸው ይመካሉ፡፡ በእምነታቸው አይደራደሩም፡፡ በሌላው እምነት ደግሞ ደባ አይሠሩም፡፡ ከክፉም ጋር አይመክሩም፡፡ የራሳቸውን እምነት በሚያከብሩት ልክ የሌላውንም እምነት ያከብራሉ፡፡ ይህ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ማንነት ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ስለማተባቸውና ስለቃላቸው የሞቱት ሞቶ ማትረፍ እንዳለ ስለሚያውቁ ነው፡፡
ጀግናው ዓፄ ቴዎድሮስ መቅደላ አምባ ላይ ሽጉጥ የጠጣው የኢትዮጵያዊነት ወኔ ስላሰከረው ነው፡፡ ሞቶ ማሸነፍን፣ ሞቶ ጠላትን ማዋረድንና ሀገርንም ማዳንን፣ እጅ ያለመስጠት ጀግንነትንም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጠራርተው ሀገር ጠብቀዋል፡፡ ሀገር አቆይተዋል፡፡ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያንስ ምን ነካቸው? “ምግባር ከዘር ይወረሳል” ይባል አልነበር? ያ መልካም ምግባር የት ገባ? የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በዘር ተጠራርተው የአንደኛውን ዘር ለማጥፋት ዶልተዋል፡፡ የማይበሉትንም የሚበሉትንም ገድለዋል፤ በአምሳያዎቻቸው ደግሞ የበለጠ ጨክነዋል፡፡ ልብ አድርግ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አልኮነንኩም፡፡ ዛሬም ሞተው ሌሎችን ያኖሩ አሉ፣ ዛሬም ደማቸውን አፍስሰው የወገንን ችግር ያነጹ አሉ፡፡ ቀደምቷ የኢትዮጵያ እናት ልጇ ጠላትን ድል አድርጎ ሲመለስ ወገኑንና ሀገሩን ሲያስከብር ደስ እያላት የደስታ እንባ አንብታ ትቀበለው ነበር፡፡
የዛሬዋ እናት መቀነቷን ዳስሳ፣ ሳይኖራት አጉርሳ ወገቧን በቀጭን አስራ ያስተማረችውን ልጅ ከወንድሙ በተወረወረ ድንጋይ ተገድሎ ሲመጣ ቀጭኑን መቀነት ፈትታ በቀጭን ገመድ ወገቧን አስራ የደም እንባ ታፈስሳለች፡፡ ዘረኝነት በሚባል ከንቱ መንፈስ የስንቱ ቤት ተዘግቷል፣ ስንቶች ሳይበሉ አድረዋል፡፡ እናትና አባት ልጆቻቸውን አጥተው ቀርተዋል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን አጥተዋል፡፡ ብቻ ያልሆነው ነገር የለም፡፡ ወይ ያጣነው ካለያም የጣልነው ነገር አለ፡፡ እንዴት አባቱና አያቱ ጠላትን መክቶ ያቆያትን ሃገር ልጁ ወንድሙን ገድሎ ለመሸጥ ይዘጋጃል፡፡ ይህ እንዴት መጣ? ትውልዱ መክኖ ነው? ወይስ ሌላ ችግር ተፈጥሮ እንዲህ የሆነው? የሃይማኖት አባቶችን አነጋግሬ ነበር፡፡ በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርትና የዳዕዋ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ አህመድ ዘይን ያሲን የቀደመውና የአሁኑ ኢትዮጵያውያን አኗኗር የተለያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገር፣ ስለ እምነትና ስለአንድነት ሲሉ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት አቅርበዋል፤ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሀገርን፣ ሃይማኖትንና አንድነትን ለራስ ጥቅም አውለዋል፤ በእነዚህ ትውልዶች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጠላት ያልደፈራት፣ ጥቁር ሁሉ የኮራባት ስለሀገሩ አንድ ዓይነት ሐሳብና አመለካከት የነበረው ሕዝብ ስለነበራት እንደሆነም ሼህ አህመድ ተናግረዋል፡፡
“ትውልዱ ከነብሱ ይልቅ ስጋውን አስቀድሟል” ያሉት ሼሁ የሰው ልጅ ስሜቱን አሸንፎ እንዲኖር ሃይማኖቱ ስለሚያዝዘው በተለይም በማኅበራዊ ሜዲያዎች የሚሠራጩትን የሀሰት መረጃዎች ከስሜታዊነት ጸድቶ መመልከትና መቀበል እንደሚገባው መክረዋል፡፡ ወደ ቀደመ ሠላማችንና አንድነታችን ለመመለስም እውነተኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማጥናት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ሙስሊም የአሠሪ ኮሚቴ አባል የሚሆንባት፣ መስጅድ ሲሠራ ክርስቲያን የአሠሪ ኮሚቴ አባል የሚሆንባት ሀገር ናት፤ ይህ ደግሞ ለዘመናት አብረን እንድንኖር ያደረገን ታላቅ እሴታችን ነው›› በማለትም ያለውን አብሮነት አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ከሙስሊሙ ወገን አንድ አጥፊ ሲፈጠር የሁሉም ሙስሊም አመለካካት መስሎት የሚሠጋ ክርስቲያን፣ ከክርስቲያኑ ወገን አንድ አጥፊ ሲፈጠር የሁሉም ክርስቲያን አመለካከት መስሎት የሚሰጋ ሙስሊም ተፈጥሯል›› ብለዋል ሼህ አህመድ፡፡
ሥረ መሠረቱ ግን ውሸት እንደሆነና የሌላ ቤተ እምነት የሚያቃጥል ወይንም የሚገድል በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የሌለ መሆኑን የሁሉም የሃይማኖት አባቶች ማስተማር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በአማራ ክልል መልካም የሆኑ ሥራዎችን እየተሠሩ እንደሆነ የገለጹት ሼህ አህመድ “ምዕመኑን ስለሠላም እና ከሌሎች ጋር ተቻችሎ ስለ መኖር እያስተማርን ነው” ብለዋል፡፡ ወደ ፊትም በሠላም፣ በአንድነትና በፍቅር ዙሪያ በትኩረት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ ገዳም አስተዳዳሪ አባ ፅጌ ሥላሴ መዝገቡ ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ልጆች መገኛ እንደሆነች አመላክተው ‹‹ሰው ከሌላው ፍጥረት የሚለየው ሰብዓዊነት ስላለው ነው›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ ሠላምና መቻቻል እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች›› ያሉት አባ ፅጌ ሥላሴ ሕዝብ የሚያስተምሩ፣ የሚመክሩ ያጠፉትን የሚገስጹ አባቶች ያሏት በመሆኗ እንደሆነም አመልተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ንጉሥ ቀብቶ እስከማንገሥ የደረሠች እንደሆነች ያመላከቱት አባ ፅጌ ሥላሴ “ሌላው ሃይማኖት በሠላምና በፍቅር ይኑር” ብላ እንደምታምን ገልጸዋል፡፡
‹‹ከሁሉም ነገር ሰውነት መቅደም አለበት፤ ሃይማኖት የሚመሠረተው ከሰውነት ነው፤ ሰው ያልሆነ ሃይማኖት የለውም፤ ሰው ሰማያዊ ዓለም እንደሌላቸው እንደ አራዊት መሆን የለበትም፤ ለምድራዊው ሳይሆን ዘላለማዊ ለሆነው ሕይወት ተገዥ መሆን አለበት›› ሲሉም ሰው በሃይማኖቱ በመጽናት ሰውነትን እንዲያስቀድም መክረዋል፡፡ ክፉን በክፉ መመለስ እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹የቀደሙት መሪዎች ‹ፈሪሐ እግዚአብሔር› የነበራቸው ናቸው፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው መሪ ደግሞ ክፉ አያደርግም፤ ለሁሉም በጎ ያስባል፤ ሁሉም በአንድነት ይከተለዋልም፡፡ የቀደሙት መሪዎች ኢትዮጵያውያንን እንደ ችቦ አንድ አድርገው አስረው ያስተዳድሩ ነበር›› በማለትም የቀደሙትን መሪዎች ጥበብ አድንቀዋል፡፡ ሕዝቡም በሥነ ምግባር የታነጸ እንደነበር ነው አባ ፅጌ ሥላሴ የተናገሩት፡፡ የዓድዋን ጦርነት እንደምሳሌነት ያነሱት አባ ፅጌ ሥላሴ መሪው ለሕዝቡ፣ ሕዝቡ ደግሞ ለመሪው ታማኝ ስለነበረ ለሀገር ጥሪ እስከሞት ደጅ ድረስ መሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአሁን መሪዎች ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ መሆን እንዳለባቸውና ደረቅ ፖለቲካ ብቻ የሚያራምዱ መሆን እንደሌለባቸውም መክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሀገሪቱን ወደ ችግር እንድትገባ አድርጓታል ብለዋል፡፡ ‹‹የሚያሳዝነው ክፉ ነገር መደረጉ ሳይሆን ለተደረገው ክፉ ነገር ሁሉም አካል ለመፍትሔው አለመዘጋጀቱ ነው›› ያሉት አባ ፅጌ ሥላሴ ሰው እስካለ ድረስ ከችግር ስለማይላቀቅ ብልሀነቱ ለችግር መፍትሔውን ማሰብ ነውም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መሪዎች የራሳቸውን ክብርና ዝና ለመጠበቅ ሲሉ የሚገጥሙት እሰጥ አገባ ዘወትር የሚገናኘውን ማኅበረሰብ እየጎዳ ነው፤ አብዛኛው ችግር የሚመነጨው ከመሪዎቹ እንደሆነም አባ ፅጌ አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትጥቋ እምነቷና አምልኮ እንደሆነ ገልፀው ሁሉም በየሃይማኖቱ በጎ ተግባር መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር በአራቱም አቅጣጫ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነት ያምናል፤ አንዳንድ ግለሰቦች ግን ከኢትዮጵያዊነትም ከሰብዓዊነትም ወርደው ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት እየፈጸሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹የታመመን ሰው ቤተሰብ ወይም ጎረቤት ወደሐኪም ቤት አለበለዚያም ወደጠበል ይወስዳልና በዘረኝነት ያበዱ ግለሰቦችን ጎረቤትና ዘመድ ሊቆጣቸው ይገባል›› ሲሉም መክረዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች በትምህርትና በጸሎት፣ መንግሥት ደግሞ የሕግ የበላይነትን በማስከበሩ በኩል በትኩረት መሥራት አለበትም ብለዋል አባ ፅጌ ሥላሴ፡፡ ሕዝቡም ቢሆን መልካም ሐሳብ ያለቸውን መሪዎች መደገፍ እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here