ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ባለፉት ሁለት ዓመታት 138 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኃይል ሽያጭ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

0
47

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 23/2012ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ 12 ከሚሆኑ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ አማራጮች 4 ሺህ 270 ሜጋ ዋት ኃይል የምታመርት ሀገር ናት፡፡ ከዚህ ግማሹን ብቻ በመጠቀም ከሀገር ውስጥ አልፋ ለሱዳን እና ለጅቡቲ የመሸጥ ዕድልም አግኝታለች፡፡ በአንፃሩ በሀገር ውስጥ በርካታ ፋብሪካዎች ከኃይል አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ እና ከፌዴራል የኃይል ተቋማት እስከ ክልል ባሉ አሠራሮች ችግር ኃይልን በተስፋ የሚጠብቁ ብዙዎች ናቸው፡፡

በከተሞች የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግር ተገቢውን ሥራ መሥራት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በከተሞች የኃይል እጥረት ችግር አለ የሚል የሕዝብ ቅሬታ ይደመጣል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ግን ሀገሪቱ ‹‹የኃይል መሠረተ ልማት ችግሮች እንጂ የኃይል እጥረት የለባትም›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ9 እስከ 13 በመቶ የሚሆን የኃይል ፍላጎት ይጨምራል፤ ይህንን ፍላጎት የሚመጥን የኃይል መሠረተ ልማቶች ማሟላትና የሚመነጨውን ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊነት ከ66 ኪሎ ቦልት በላይ የሆኑ የኃይል ተሸካሚና ሰብስቴሽኖችን ማስተዳደር ነው፡፡ ‹‹ወደ ውጭ የሚላከው ኃይል ኢትዮጵያውያን በማይጠቀሙበት የእረፍት ሰዓት ነው›› ብለዋል አቶ ሞገስ፡፡
አቶ ሞገስ ኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ሩብ ዓመት ድረስ ለሱዳን እና ጅቡቲ በሸጠችው የኤሌክትሪክ ኃይል 138 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዳገኘች ተናግረዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ኃይል 69 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ በ2011 ዓ.ም 963 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኪሎ ዋት በመሸጥ 55 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች፡፡ በ2012 የበጀት ዓመት በአራት ወራት ደግሞ 217 ነጥብ 2 ሚሊዩን ኪሎ ዋት በመሸጥ 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቱን የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

2011 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተፈጠረ የኃይል እጥረት ምክንያት ከግንቦት እስከ መስከረም አጋማሽ ለሱዳን ኃይል አለመቅረቡንና ለጁቡቲ ደግሞ በግማሽ መቀነሱን ነው አቶ ሞገስ የተናገሩት፡፡

አቶ ሞገስ መኮንን ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ለጅቡቲ የምትሸጠው ኃይል የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በመቀነስ ባለመሆኑ ሕዝቡ ስጋት ሊኖረው እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here