‹‹እኛ ከሌለን መንግሥት የለም እና እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የለችም የሚሉ ድምፆች ትክክል አይደሉም፡፡›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር)

0
32

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ፈተና አልባ ሳይሆን ስኬታማ ምርጫ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ በሀገሪቱ ያሉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የ2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ እና የመሪ ድርጅቱ ኢህአዴግ ውህደት ይጠቀሳሉ፡፡ “በምርጫ አዋጁ ላይ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ስምምነት ሳይፈጠር፣ በመሪ ድርጅቱ ኢህአዴግ ውስጥ ያለው ውህደት ሳይቋጭ እና በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ወቅቶች ለሚከሰቱ አለመግባባቶች አማራጭ መፍትሄ ሳይቀመጥ ምርጫ ማካሄድ ተገቢ ነው ተብሎ ይታሰባል?” የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በምክር ቤት አባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምርጫውን ዘንድሮ አሳልፈን በሚቀጥለው ዓመት ብናደርገውም ችግር አልባ ምርጫ ማካሄድ አንችልም፤ የተሻለው ነገር ዴሞክራሲ የልምምድ ውጤት ነውና እንከን አልባ ሳይሆን ስኬታማ ምርጫ ለማድረግ መስራት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡ ለምክር ቤቱም ሆነ ለመንግስት አካላት ከሕዝብ ይሁንታን አግኝቶ መሥራት የተሻለ በመሆኑ ምርጫው መካሄድ እንዳለበት እንደሚያምኑም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡

የምርጫ ቦርድ በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ እና በበጀት ካለፉት ዓመታት በተሻለ ተደራጅቷል፡፡ ይህ መንግስት ለምርጫው ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት ቁርጠኝነት ምርጫ ቦርድን በሚፈለገው ደረጃ ማሟላት ብቻ ሳይሆን በምርጫ ሌላ አካል አሸናፊ ከሆነ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ለማስረከብም ቁርጠኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በምርጫ አዋጁ ላይ በተወሰኑ ፓርቲዎች ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ሲሰጡም የምርጫ አዋጁ በምርጫ ቦርድ አባላት ተረቅቆ በምክር ቤት አባላት እንዲፀድቅ የተደረገው እና የመንግስት የካቢኔ አባላት ያልተወያዩበት መንግስት ራሱን ገለልተኛ ለማድረግ ስለፈለገ ነው ብለዋል፡፡ የምርጫ ሙሉ ቅርፅ፣ አሸንፎ መንግስት መሆን ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተፎካካሪ ሆኖ የተወሰኑ ወንበሮችን ለመያዝ እና ይህ ካልተሳካ እንኳን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሃሳብን ሽጦ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከዓለም እና ከራሱ ታሪክ የተማረ ሕዝብ በመሆኑ ፍላጎቱ በምርጫ የሚፈልገውን አካል መምረጥ እንጂ ምርጫን አስታክኮ ግጭት መፍጠር ባለመሆኑ ስጋት የለም ባይባልም መቋቋም የሚችል ሕዝብ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ በተወሰነ ደረጃ መገራት የሚሻ ነፃ ሚዲያ ስላለ በጋራ ትብብር መሥራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ከኢህአዴግ ውህደት ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውህደቱ ባለፉት 10 ዓመታት በድርጅቱ ጉባኤ ሲነሳ የነበረ፣ ጥልቅ ውይይቶች እና ሰፊ ጥናት የተካሄደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ከሌለን መንግስት የለም፤ እና እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የለችም የሚሉ ድምፆች ትክክል አይደሉም፤ ኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ ሳይኖሩ ነበረች›› ብለዋል፡፡

ውህደቱ በውይይት ላይ እንደሆነ ያስገነዘቡት ዶክተር ዐብይ ሃሳብ ያለው ሀሳቡን ይዞ ይምጣና ይወያይ ያልፈለገ ደግሞ ከውህደቱ ይወጣል ነው ያሉት፡፡ በውህደቱ ጉዳይ ውይይቱ ሲጠናቀቅ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብ እና ምክር ቤቱ ውሳኔውን እንደሚያሳርፍ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here