ከከንፈር መምጠጫነት እስከ አርዓያነት፡፡

0
1419

የካቲት አንድ ቀን በዕለተ ማክሰኞ 1979 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ቀበሌ አስር አንድ ሕጻን ይህችን ምድር ተቀለቀለ፡፡ ቤተሰቦቹም ልጅ ለመውለድ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ የሕጻኑን መወለድ በእልልታና በፌሽታ ፈጣሪን በማመሥገን ተቀበሉት፡፡

በልጅነቱ ቤተሰቦቹ ወደ ወረታ መጥተው መኖር ጀመሩ፡፡ በጉግት ያገኙትን ልጅ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረጉለት ማሳደጋቸውን ቀጠሉ፤ ስሙንም ከማል ቃሲም አሉት፡፡ ከማል ቃሲም የልጅነት ጊዜውን ከጎረቤት ልጆች ጋር በመሆን የዕቃ ዕቃ፣ ድብብቆሽ፣ አባሮሽ፣ ሌባና ዱላ የመሳሰሉ የልጅነት ጨዋታዎችን እስከ ስድስት ዓመቱ ይጫወት ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ግን በከማልና በቤተሰቦቹ ላይ ደስታን የሚነጥቅ አንድ አስደንጋጭ ነገር አጋጠመ፡፡ በደርግና ኢሕአዴግ  ጦርነት ወቅት በወረታ ከተማ ተበላሽቶ የቀረ ታንክ ነበር፡፡ በዚህያ የቆመ ታንክ ላይ ከእኩያዎቹ ጋር በጨዋታ ላይ እያለ እግሩን ወደ ታንኩ ውስጥ በማስገባቱ ከባድ አደጋ እንደደረሰበት የእንባ ሲቃ እየተናነቀው ከማል አጫወተኝ፡፡ በዚህ ምክኒያት ቃለ መጠይቃችንን ለአፍታ ገታ አድርገን ነበር፤ ግን ከማል ሲረጋጋ  ጨዋታችንን ቀጠልን፡፡የልጅነት ጊዜውን እንደጓደኞቹ እንደፈለገ በመዝለል የደስታ ጊዜውን ሳያሰልፍ መቅረቱና እንዲህ ፈጣሪውን ለምነው ያገኙት ልጅ እንዲህ ዓይነት ክስተት በመፈጠሩ እጅግ አዘኑ፡፡

የከማል ቤተሰቦችም እግሩ ላይ በደረሰበት ቁስለት የሕክምና ዕርዳታ ተደርጎለት ወደ ቀድሞው ጤንነት ይመለሳል በሚል ተስፋ ወደ ተለያዩ የሕክምና ተቋማት ቢወስዱም የደረሰበት አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ አንድ እግሩ በሕክምና እንዲወገድ የሕክምና ባለሙያዎች ወሰኑ፡፡

አሁንም ለከማል ቤተሰቦች ሌላ ፈተና ሆነባቸው፤ እውነታውን አምነው ለመቀበል ተቸገሩ፤ ነገር ግን ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ በሕክምና ባለሙያዎች ሐሳብ ተስማሙ፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ በእንቦቅቅላው ከማልና ቤተሰቦቹ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና አሳርፎ ነበር፡

‹‹በወቅቱ በአካባቢው የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው ስላልነበረ የአካባበው ሰዎች ባዩኝ ጊዜ ሁሉ ከንፈር በመምጠጥ ያዝልኝ ነበር፤ ይህ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ከመሆኔ ባለፈ ሌላ የሥነ ልቦና በሽታ ሆኖብኝ ነበር›› ብሏል ከማል፡፡

‹‹ዕድሜየ ለትምህርት እንደደረሰም በክራንች በመጠቀም እየተንቀሳቀስኩ ወደ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ትምህርት ቤትም ከልጆች ጋር እንደፈለኩ መዝለል አልቻልኩም ነበር፡፡ ባሕሪየም ተቀየረ፤ እጅግ ተንኮለኛ፣ ረባሽና ለአስተማሪዎቼ ሁሉ የማልታዘዝ ልጀ ሆንኩ›› ብሏል ልጅነቱን ተመልሶ ሲያስታውስ፡፡

ከማል ራሱን አሳምኖ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የተሳሳተ አመለካከት በመስበር ዕውቀት ገብይቶ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ሀ ሁ ሲጀምር ‹‹ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው ሁሉ ቤተሰቦቹ ባለመግባባታቸው ተለያዩ፡፡ የወላጆቹንም ፍቅር አጣ፡፡ አንድ ጊዜ ወደ አባቱ ሌላ ጊዜ ወደ እናቱ ሲል ስድስተኛ ክፍል ደረሰ፡፡ አስቸጋሪ ኑሮ ለሚገፉት እናቱም ሌላ የቤት ሥራ ሆኖባቸው እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ከማል ለትምህርት ብዙም ትኩረት ስለማይሰጥ 8ኛ ክፍልን ሁለት ጊዜ መድገሙን ያስታውሳል፡፡ ለ3ኛ ጊዜ ለመማር ቢፈልግም በወቅቱ ለ3ኛ ጊዜ 8ኛ ክፍል በመደበኛ መርሀ ግብር (በቀን) መማር ስለማይፈቀድና ቀን መማር ስላልቻለ የማታ ትምህርቱን ተከታትሎ ወደ ዘጠነኛ ክፍል አለፈ፤ እንደገናም ወደ ቀኑ መርሀ ግብር ተዛውሮ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ለወጣት ከማል የኑሮ መሠረቱ የሆነው የቴኳንዶ ስፖርት ፍቅር ያደረበት፡፡ አንድ የክፍል ጓደኛዬ በአጋጣሚ የቴኳንዶ ስፖርት ይሠራ ስለነበር ‹‹እኔ እየሠራሁ ነው ለምን አንተስ አታየውም? ታየውና ከወደድከው ትጀምራለህ›› ብሎ ይዞት እንደሄደ ያስታውሳል፡፡

‹‹ስፖርት ቤት ገባን፤ ለእኔም አግዳሚ ወንበር ተሰጥቶኝ ተቀምጬ በግርምት እጄን አፌ ላይ በማድረግ ለሁለት ሰዓታት ያህል  ተመለከትኩ፡፡ ከተመሰጥኩበት ነቃ ስል ዛሬ አካሌ ቢጎድልም ሙሉ አካል ካለቸው ሰዎች በላይ እንድሆን ያደረገኝ አሰልጣኝ መምህር ቴወድሮስ ምሕረት ‹ስፖርቱን እንዴት አየኸው?› አለኝ፡፡ እኔም በቁጭት እግር ቢኖረኝ ኖሮ እኔም እሠራ ነበር አልኩት፡፡

መምህሩም የ‹ፊዚዩ ቴራፒ› ባለሙያም ነበር፤ ወዲያዉኑ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይጠይቀኝ በነፃ ልምምዴን እንድቀጥል ዕድሉን አመቻቸልኝ፡፡ በልምምድ ወቅት ክራንቹ እየተሰበረና እያተንሸራተተ በጣም አስቸግሮኝ ነበር እንጂ ሌላ ያጋጠመኝ  ችግር የለም፡፡ ስፖርት መጀመሬን ቤተሰቦቼ አያውቁም ነበር፡፡ እናቴ እንኳን አብራኝ እየኖረች አታውቅም ነበር›› ብሏል፡፡

ስፖርቱን ሲሠራ የስፖርት ጥበብ ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር ትምህርትም ይሰጥ ስለነበር በባሕሪ አስቸጋሪ የነበረው ልጅ አደብ መግዛቱን ይናገራል፡፡ ስፖርት መሥራቱንም ለእናቱ የነገራቸው የምርቃኑ ዕለት ነበር፡፡ በዕለቱ ሁለቱም ተቃቅፈው በእንባ ተራጩ፡፡ እናቱም ወደ ስፖርት ቤት መጥተውም አስመረቁት፡፡ ከዚያ እናቱ በተሠማራበት ሥራ እንዲበረታ ማበረታታቸውን ቀጠሉ፡፡

‹‹የአካባቢው ማኅበረሰብ አመለካከት ስላልተቀየረ አንተ በአንድ እግርህ ቴኳንዶ ሠርተህ የት ልትደረስ ነው? እያሉ ለማሸማቀቅ ይሞክሩ ነበር፤ ነገር ግን ለእነዚህ ኋላቀር አመለካከቶች ሳልበገር ሙሉ አካል ካላቸው ሰልጣኞች ጋር በ2002 ዓ.ም በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በጥቁር ቀበቶ ተመረቅሁ›› ብሏል፡፡

ከጎንደር ወደ ወረታ በመምጣትም የግሉን ቴኳንዶ ስፖርት ማሰልጠኛ በመክፈት በርካታ ወጣቶቸን ከሱስ በማውጣት በዘረፉ በክልልና ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

እስከ ሰባት ዙር በባሕር ዳር አምስት ሺህ ስፖርተኞችን አሰልጥኖ ማስመረቅ የቻለው ከማል በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ሁለት ዙር አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 15 ከወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ተከራይቶ የሚሠራው ከማል በከተማው አሉ ከሚባሉ የቴኳንዶ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከልም አንዱ ነው፤ በአካልና በሥነ ምግባር የታነፁ ስፖርተኞን በማፍራት ላይም ይገኛል፡፡

ወጣት ከማል በክልልና ሀገር አቀፍ በተደረጉ የፓራ ኦሎምፒክ ውድድሮች በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በመሳተፍ በርካታ ሜዳሊያዎች ባለቤት ለመሆንም በቅቷል፡፡

ለወደፊት በክልልና ሀገር አቀፍ ደረጃ በሥነ-ምግባራቸው የተመሠገኑ ብቃት ያላቸዉን የቴኳንዶ ስፖርተኞን ለማፍራት ዕቅድ እንዳለውም ተናግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ የጎዳና ተዳደሪ ልጆችን በነጻ ለማስተማር እቅድ ይዟል፡፡

ዕቅዱ እንዲሳካም ከተማ አስተዳደሩና ስፖርት ኮሚሽን የቴኳንዶ ስፖርትን እንደ ሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዘርፎች ቆጥረው ትኩረት በመስጠት ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የሰብዓዊነት ተምሳሌቱ ከማል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው የቆዩ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ያለምንም ክፍያ እያሰለጠናቸው ነው፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎቹም ከነበረባቸው ሱስ  ወጥተው ሥነ ምግባራቸው ተስተካክሏል፤  ከሱስ ነጻ የሆነ ሕይወት እንዲኖሩ መሠረት እንደሆናቸውም ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ መካካልም ቤተልሔም ውበት አንዷ ናት፡፡ ቤተልሔም ዕድሜዋ 19 ዓመት ነው፤ ስልጠና ከጀመረች አንድ ዓመት እንዳለፋት ትናገራለች፡፡ ‹‹ወደ ስፖርት ቤት ሳልመጣ ቤት ውስጥ በባሕሪዬ እጅግ አስቸጋሪ ልጅ ነበርኩ፡፡ ለቤተስብ ያለመታዘዝ እና አልፎ አልፎ የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው ልጆች ጋር አልባሌ ቦታዎች እውል ነበር፤ ወደ ስፖርት ቤት ከገባሁ በኋላ ግን የሥነ ምግባር ትምህርትም ከስፖርቱ ጎን ለጎን ስለሚሰጠን ብዙ የባሕሪ ለውጥ አሳይቻለሁ፡፡ ሰውነቴም ከልክ  ያለፈ ወፍራም ነበርኩ አሁን አቋሜም ተስተካክሎልኛል›› በማለት ተናገራለች፡፡ ወጣቶች በሱስ ተጠምደው አልባሌ ቦታ ከሚያሳልፉ ስፖርት ቤት ገብተው በአካልም በሥነ ምግባርም ቢታነፁ መልካም እንደሆነም ትመክራለች፡፡

ሌላው ሰልጣኝ ተሰፋ አገኝ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ነው፤ ወደ ስፖርት ቤት ከመግባቱ ቀደም ብሎ ካለበት የባሕሪ ችግር ከቤተሰቦቹ ጋር ባለመግባባቱ  ተለያይቶ ኑሮውን በጎዳና ላይ ይኖር እንደነበር ተናግሯል፡፡

አቶ ተስፋ በጓደኛው አነሳሽነት ወደ ስፖርት ማሰልጠኛ መግባቱን ተናግሮ በየቀኑ ከስፖርት ስልጠና በተጨማሪ ለ20 ደቂቃ ያህል የሥነ ምግባር ትምህርት ስለሚሰጥ ባሕሪው ተስተካክሎ ቤተሰቦቹን ይቅርታ ጠይቆ በመመለስ እየተማረ  ቤተሰቦቹንም እየረዳ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ‹‹ሌሎች ወጣቶችም ካለባችሁ ሱስ በተለይም አሁን አሁን እየተበራከተ መጥቶ በበርካታ ሰዎች ላይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ችግሮችን እያስከተለ ካለው የስፖርት ቁማር ተላቅቀው በስፖርት ማዘውተሪያ ላይ ቢያሳተፉ ጥሩ እንደሆነ እመክራለሁ›› ብሏል::

በአማራ ክልል የፓራ አሎምፒክ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የቴክኒክ ባለሙያ አቶ የሺዋስ ጌታሁን በክልሉ ከሚገኙ የተሻሉ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ተቋማት በገንዘብና በቁሳቁስ ለመደገፍ ባይቻልም በስልጠና የማገዝ ሥራዎች ግን እየተሠሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑም በቅርብ ጊዜ እንደገና በአዲስ መልክ ስለሚደራጅ የክትትትልና ድጋፍ ሥራዎች ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽንና ከባሕር ዳር ከተማ አስተደዳር ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ወጣት ከማልም በራሱ ጥረት በስፖርት ዘርፈ ተሰማርቶ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝ በመሆኑ የማበረታቻ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ዘርፉ እንደአንድ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሆኖ እንዲያገለግልም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የጋራ ዕቅድ ወጥቶ ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንም አቶ የሺዋስ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደረጀ ጀርባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here