ከወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ቆይተው ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓዙ መንገደኞች በትራንስፖርት እጥረት እየተቸገሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡

0
49

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከአድያመ ዮርዳኖስ ወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ጸበል ቆይተው በጭስ ዓባይ ከተማ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ለአብመድ አስታውቀዋል፡፡ በጸበልተኞቹ መብዛት ቦታው ከፍተኛ የሰዎች ጥግግት የሚታይበት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ ይህ ደግሞ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የወቅቱን የኮሮ ቫይረስ ወረርሽኝ በመስጋት ፀበልተኞቹ ከነበሩበት ገዳም ወደየአካባቢያቸው እየሄዱ ነው፡፡ በተለይ ወደ ባሕርዳር ከተማ ለመጓዝ የፈለጉ መንገደኞች እንደተናገሩት አገልግሎቱን ለማግኘት ለቀናት ጥረት ቢያደርጉም መፍትሔ አላገኙም፡፡ ወደ ጭስ ዓባይ ከተማ ብዙ ሰዎች መግባታቸውን ተከትሎም መጨናነቅ እንደተፈጠረ ነው የተናገሩት፡፡ በቶሎ ወደ ቤታቸው መሄድ ባለመቻላቸውም በአካባቢው የመኝታ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት እንደተቸገሩም አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ እጥረቱ የተፈጠረው አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩ ከ30 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማጓጓዝ በመሠማራታቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
በተለያዩ ተቋማት ለመንግሥት እና ለልማት ድርጅት ሠራተኞች “ሰርቪስ” የሚሰጡ ተጨማሪ 22 ተሽከርካሪዎችም እጥረት ወደ ተከሰተባቸው ቦታዎች በፍጥነት እንዲሠማሩ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ በሁለቱም መናኸሪያዎች ወደ ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች ስምሪት ይሰጡ ከነበሩ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተወሰኑት እጥረት ወደታየበት አካባቢ እንዲሠማሩ መደረጉንም በቢሮው የትራንስፖርት ስምሪት ባለሙያ አቶ ጌታቸው መርሻ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ እንደሚቀረፍም ነው ባለሙያ የተናገሩት፡፡

በጉዞ ወቅት መተፋፈግ እንዳይኖር ለማድረግም አነስተኛ የመጫን አቅም ያላቸው ስምንት ሰዎችን፣ ከፍተኛ የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎች ደግሞ አንድ፣ አንድ ወንበር እያለፉ እንዲጭኑ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ከክልሎች የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መምከራው ታውቋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በትራንስፖርት ዘርፉ የተጀመሩ ተግባራት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በተዳሰሰበት የቪዲዮ ኮንፈረንስ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ችግሩን መቅረፍ በሚቻልበት ዙሪያ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here