ከ123 ሄክታር መሬት በላይ የማልማት አቅም ያለው የመስኖ ፕሮጀክት ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡

0
28

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ በግብርና ዕድገት ፕሮግራም በ2010 ዓ.ም የግንባታ ሥራው የተጀመረው የመስኖ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል፡፡

በወረዳው አደጋ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ጌታው ገድብ የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው አርሶ አደሮች መካከል ናቸው፤ የመስኖ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ያለአገልግሎት ሲፈስ የነበረውን ውኃ ለእርሻ ሥራቸው እንዲጠቀሙ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ጠቃሚ መሆኑን የተናሩት አርሶ አደሩ ‹‹የተሠራውን ግድብ በማኅበር ተደራጅተን እንጠብቃለን›› ብለዋል፡፡ በፊት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የዝናብ ውኃ ጠብቀው ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ እንደሚያግዛቸውም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ሠርቶ የማስረከብ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ እኛ ደግሞ በአግባቡ ይዘን መጠቀም አለብን›› ብለዋል አርሶ አደሩ፡፡

የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው መንግሥት ለአብመድ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ መስኖው ከ210 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክቶች 123 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በወረዳው በመገንባት ላይ የሚገኙ ሰድስት ተጨማሪ የመስኖ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አቶ ቻላቸው መንግሥት አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here