ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረው ተጨማሪ 28 ሚሊዮን ብር ለማጭበርበር ሂደት ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥ ሥር ዋሉ፡፡

0
33

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የተሰረቁ ቼኮችን እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከመንግሥትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎች በሕግ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በተጠርጣሪ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ሊወሰድ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እየተፈፀመ ስለመሆኑ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ የምርመራና የክትትል ቡድን በማዋቀር ምርመራው እንደተጀመረ በኮሚሽኑ የከባድ ሌብነትና ዘረፋ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ ዓለማየሁ አስታውቀዋል፡፡
በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙት ከ70 በላይ ግለሰቦች ከተለያዩ የግል ተቋማት የባንክ ቼኮችን በመስረቅ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከተለያዩ የግል ባንክ ደንበኞች የባንክ ሒሳብ ውስጥ 60 ሚሊዮን 843 ሺህ 601 ብር ወጪ አድርገው መውሰዳቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
በተመሳሳይ መንገድ ወጪ ተደርጎ ሊወሰድ በሂደት ላይ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለና ከተጠርጣሪዎቹ እጅ የተለያዩ የባንክ ቼኮች እና ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች እንደተያዙ የገለፁት ኢንስፔክተር ያሬድ በተጠርጣሪዎቹ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ውስጥ የተገኘ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገድ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት ከኢትዮ-ቴሌኮም፣ ከባንኮች፣ ከወረዳ አስተዳደር፣ ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ሠራተኞች ተባባሪ የሚሆኗቸውንና መረጃ የሚሰጧቸውን አንዳንድ ሠራተኞች ለእኩይ ተግባራቸው በመመልመል ነው፡፡

ቼክ ተሰርቆባቸው 5 ሚሊዮን ብር ከባንክ ሒሳባቸው ወጪ የተደረገባቸው አቶ እያሱ ተቋመ እና በሀሰተኛ የውክልና ሰነድ 700 ሺ ብር የተወሰደባቸው ወይዘሮ ፍቅርተ ኃይሉ እና ባለቤታቸው አቶ ልዑል አዲሱ ስለተፈፀመባቸው ወንጀል ለፖሊስ ማገራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here