ወልድያ ኮሮናን የናቀች ትመስላለች፡፡

0
43

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰሜን ወሎ ዞን ርእሰ መዲና ወልድያ የአማራ ክልል የንግድ ትስስር ድልድይ እና የእርስ በርስ ግንኙነት ኮሪደርም ሆና ታገለግላለች፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ውሎ ቢያድርም ለወልዲያ እና አካባቢዋ ስጋት ያልሆነ ይመስል መዘናጋቶች አብዝተው ይስተዋላሉ፡፡ ምንም እንኳን ስለበሽታው አስከፊነት ከብዙኃን መገናኛ መልእክቶች እስከ ኢትዮ-ቴሌኮም ማስታዎቂያዎች፣ ከቀይ መስቀል ቅስቀሳ እስከ ታላላቅ ባነር መግለጫ፣ ከጤና ተቋማት አስተምህሮ እስከ ወጣቶች የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች መልእክት ተደጋግሞ እየተሠራጨ ቢሆንም አስፈላጊው ጥንቃቄ ሲደረግ ግን አይስተዋልም፡፡

በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የወጣት መዝናኛ ቤቶች (ጌም ዞን) በቂ አየር በሌለበት ሁኔታ በርካታ ቁጥር ባላቸው ወጣቶች ታጭቀው ይስተዋላሉ፡፡ የአካላዊ ርቀት ፈፅሞ አይስተዋልም፤ ሠላምታ መለዋወጡ እንደነበር ነው፡፡ በምሽት ቤቶች፣ በመዝናኛ ቦታዎች ላይም ከቀድሞው የተለየ ነገር አይስተዋልም፡፡ ለምን አስፈላጊው ጥንቃቄ አልተደረገም ስንል የከተማዋን ነዋሪዎች አነጋግረናል፡፡

በወልድያ ከተማ ነዋሪ እና የባጃጅ አገልግሎት ሰጪው ወጣት ሲሳይ ፈቃዴ ስለኮሮና ቫይረስ አስከፊነት መረጃዎች በበቂ ሁኔታ መዳረሳቸውን ገልፆ በከተማዋ ነዋሪ የሚደረገው ጥንቃቄ ግን አነስተኛ መሆኑን ነግሮናል፡፡ አስፈላጊው ጥንቃቄ የማይደረግበት ምክንያት ከልማዳዊነት አለመውጣት እና ሁሉንም ለፈጣሪ ከመስጠት የመነጨ እንደሆነ አስተያዬት ሰጪው ነግሮናል፡፡
“የጥንቃቄ ጉድለቱ የመነጨው የችግሩ ምንጭ የፈጣሪ ቁጣ ተደርጎ መወሰዱ ነው” ያለችን ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ገነት ሰጠኝ ናት፤ መፍትሔውም አምልኳዊ ብቻ እንደሆነ በማኅበረሰቡ እንደሚታመን ተናግራለች፡፡ ሠላምታ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለየ ቦታ አለው፤ ይህም በቀላሉ የሚቀር ሳይሆን ተደጋጋሚ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚፈልግ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

“በከተማዋ የሚገኙ ባንኮች፣ የአውቶቡስ መናኸሪያ እና በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ የንጽሕና መጠበቂያዎች ተቀምጠዋል” ያሉን ደግሞ የወልድያ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፈንታው ስጦታው ናቸው፡፡ ቫይረሱ በከተማዋ ውስጥ ከተከሰተ የማቆያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንም ነግረውናል፡፡ የቤት ለቤት ቅስቀሳ፣ የጤና ተቋማት አስተምህሮ እና የወጣቶች በጎ አድራጎት ተግባራት በተቀናጀ መልኩ ሥራ እንደሚጀሩም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከወልዲያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here