ዐይኖች ሁሉ ባሕሩ ላይ ናቸው፤ የጥምቀቱን ምሥጢራት ለማዬት፡፡

0
204

ባሕር ዳር፡- ጥር 11/2012ዓ.ም (አብመድ) ከሌላው ዓለም በተለየ የ13 ወራት ጸጋ የተጎናጸፈች፣ የሕዝቦቿ ኩራትና መከታ ሰንደቋ በሰማይ ላይ የሚውለበለብባት፣ ክብሯ በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ከፍ ያለች ሀገር-ኢትዮጵያ፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ እሴቶች ለማወቅ ከመሻት አልፎ የመንፈሱ ማደሻ፣ የምሥጢራትም መመርመሪያ ማድረግ ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ወርኃ ጥር ሲመጣ ደግሞ የዓለም ዐይኖች ሁሉ ወደ ባሕሩ ይመለከታሉ፡፡ ከባሕሩ ዙሪያ በሚገኘው ደግ ምዕመን ሥርዓት እየተመሰጡ ለነፍሳቸው ሐሴትን ይሸምታሉ፡፡ ጥምቀት ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም የኢትዮጵያውያን የጥምቀት ሥርዓት ግን በእጅጉ ይለያል፡፡ ለዚያም ነው ዩኔስኮ የተለዬ ሲል በዓለም ቅርስነት የመዘገበው፡፡

የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኒዓለም ዋና አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ሥርዓት ምክንያት በማድረግ እንደሚከበር አስረድተዋል፡፡ በ30 ዓመቱ የተጠመቀበትን ምክንያት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ እንዲህ ያስረዳሉ፤ “የሰው ልጅ አባት አዳም ሲፈጠር ክፉና ደጉን የሚያገናዝብ የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ በገነት ተቀመጠ፤ በኋላም በሰይጣን አሳሳችነት ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሶ ወደ ሲዖል ወረደ፤ ክርስቶስም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ሲመጣ አዳም በተፈጠረበት ዕድሜ ዳግም ልጅነቱን ይመልስለት ዘንድ 30 ዓመታትን ጠበቀ፡፡ በ30 ዓመቱም ተጠምቆ ልጅነቱን መለሰለት፡፡ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋንም በተፈጠረች በ80 ቀኗ ልጅነትን ተቀብለው ወደ ገነት ገቡ፡፡ ይህን ለመዘከርም ክርስቲያን ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው፣ ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ተጠምቀው ክርስትና ይነሳሉ፡፡’’

ይህንንም ጥምቀት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ “የ40 እና የ80 ቀን ጥምቀት ረቂቅ፣ መንፈሳዊ ልደት ነው” ይሉታል፡፡ አዳም ሔዋንን በሚስትነት የተሰጠው በ80 ቀኗ ስለነበር በዚህ መነሻነት የሰው ልጅ ‘የ80 ሚስቴ’ እያለ በሰማኒያ ሕግ አግባብ እንደሚጋባ ሊቀ ሊቃውንት ገልጸዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ለምን ተጠመቀ? ስንልም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራን ጠይቀናቸዋል፡፡ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም “ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን ካሳሳተ በኋላ ‘አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ’ የሚል የዕዳ ደብዳቤ በመጻፍ አንዱን በባሕረ ዮርዳኖስ፣ ሌላኛውን ደግሞ በሲዖል አስቀመጠው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የሰይጣንን ሥራ ለመደምሰስ ነበርና የመጣው በጥምቀቱ የመጀመሪያውን ደብዳቤ ለማጥፋት ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ወረደ፤ በባሕረ ዮርዳኖስም የእዳ ደብዳቤው ከተቀመጠበት ላይ ቆመ፡፡ ዮሐንስንም እንዲያጠምቀው ጠራው፡፡ በባሕረ ዮርዳኖስ የተቀበረውን የእዳ ደብዳቤም እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጠፋው” ነው ያሉት፡፡


ጥምቀት በክብር መዝገብ ላይ ያረፈው ጥንት መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ሊቃውንቱ የጥምቀትን ጥንታዊነትም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም የተለዬ ክብር እንዳላት፣ የተለየ አምላካዊ ፍቅር እንዳላት፣ ከዓለም የተለየ ለዚህ በዓል ክብር እንደሰጠች፣ የበረከት ሀገር መሆኗን እንደሚያሳይ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አስረድተዋል፡፡ ይህ አምላካዊ ቅርስ የሆነ ታላቅ ትውፊት ለሀገሪቱ ታላቅ ዕውቅና የሰጠ ነውም ብለዋል፡፡ ጥምቀት ለአማኞቹ ከልብ የመነጨ ክብር፣ ከልብ የመነጨ ፍቅር፣ ከልብ የመነጨ በዓል እና ትክክለኛ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚከበር በመሆኑ ዓለማቀፋዊ ዕውቅናው እንደተሰጠውም አበው ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ለእሴቱና ለሃይማኖቱ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም መክረዋል፡፡ እነሆ ለጥምቀት በዓል እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ እየተመሙ ነው፡፡ የዓለም ዐይኖች ሁሉ ወደ ባሕሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖቱ ተከታዮችም በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፡፡

 

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here