የሕዝብ ጥያቄዎች ለአሸባሪዎች ዓላማ ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ አገራቱ የውስጥ ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸው ኢጋድ አስገነዘበ።

0
48

የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ሠላም ለማረጋገጥ አገራቱ የውስጥ ችግሮቻቸው ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አስታውቋል።

የኢጋድ የሠላምና ፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቀጣናው ያለው የአሸባሪነት ተግባር በአዲስ መልክ እየተነሳሳ እንደሆነ ገልፀዋል። ለዚህም በተለይም በቀጣናው አገራት ውስጥ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጥያቄዎችን እንደ ምቹ ሁኔታ የመጠቀም አዝማሚያ እየታየ እንደሆነ ነው ያስታወቁት። ኢጋድ አካባቢያዊ የሠላምና ፀጥታ ሁኔታውን በየጊዜው እንደሚከታተልና ተጋላጭነቱንም እያጠና መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በቀጣናው ያለው የአልሸባብና የዳኢሽ እንቅስቃሴ ከአሁን ቀደም በሶማሊያ ብቻ የነበረውን ትኩረቱን ወደ አጎራባች አገራት እያሰፋ ለመሆኑ በቅርብ ጊዜ በአሸባሪ ቡድኑ የተመለመሉ ኢትዮጵያዊያን መያዛቸውን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል። በዚህ ወቅት በአካባቢው ህገወጥ የመሳሪያና የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ ንግድና በየቦታው ትንንሽ የሚመስሉ ህገወጥ ቡድኖች መታየታቸው ለአሸባሪ ቡድኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስለሚሆን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

“በኢጋድ በኩል የአሸባሪ ቡድኖችን እንቅስቃሴና የሽብር እቅድ የማጥናትና የመከታተል እንዲሁም መከላከያ የሚሆን አሰራርና ፖሊሲ የመቅረፅ ስራ እንሰራለን” ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት ግን የአገራቱ የተናጠልና የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በየአገራቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጥያቄ ይዘው የሚፈጠሩ ህገወጥ የታጠቁ ቡድኖችን እንደ ማስፈፀሚያ እንዳይጠቀም አገራቱ የውስጥ ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።

በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ አህጉር እንደ ትልቅ አጀንዳ ተይዞ እየተሰራበት ያለው የኢኮኖሚ፣ የንግድና የትራንስፖርት ትስስርን እውን ለማድረግም ከምንም በላይ የሠላምና ፀጥታ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም መክረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here