የመሠረተ ልማት አለመሟላት በገነቧቸው ቤቶች እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው በቻግኒ ከተማ በማኅበራት የተደራጁ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

0
39

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ቻግኒ ከተማ አስተዳድር በማኅበራት ቤት የገነቡ ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል፡፡

ነዋሪዎች ቤቶችን ከገነቡ ዓመታት ቢቆጠሩም መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ አሁንም በኪራይ ቤት ለመኖር እንደተገደዱ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ከቻግኒ ከተማ አስተዳድር ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስተራክሽንና አገልግሎት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በ85 ማኅበራት የተደራጁ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች የቤት መስሪያ ቦታ አግኝተዋል፡፡

አስተያዬታቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሰጡት የዕድሉ ተጠቃሚዎች ቤታቸውን ከገነቡ ከ2 እስከ 3 ዓመታት ቢቆጠሩም ለመኖሪያነት እየተገለገሉበት አይደለም፡፡ ይህም ላልተፈለገ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመንገድ፣ የውሃና የመብራት መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽንና አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሥራአስኪያጅ አቶ አዲሱ ካሴ ለአብዛኛዎቹ የማኅበራት ቤቶች የመንገድና የውሃ መሠረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም የመብራት ችግር ግን ብዙ በጀት የሚጠይቅ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም 40 በመቶውን ወጪ ማኅበራት እንዲሸፍኑ በማድረግ በተደራጁበት ቅደም ተከተል ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍና በመንግስት የተቀናጀ በጀት በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሁሉንም ማኅበራት የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራም አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
ከተማ አስተዳድሩ በተያዘው በጀት አመትም ለ13 ማኅበራት የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here