የመስቀል በዓል በአዊ

0
154
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2012 ዓ/ም (አብመድ) የመስቀል በዓል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚከበሩ በዓላት መካከል ዋነኛው ነው፡፡ በዓሉን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት የሚጀመረው ከአዲሱ ዓመት ማግስት ነው፡፡
 
ወንዶች ‹ባላፉቺ› እና ግንድ ይቆርጣሉ፡፡ ባላፉቺ ማለት የምሳና እና የውልክፋ እንጨት ከእነ ቅርንጫፉ ተቆርጦ ከቤት ደጃፍ ምሰሶ እና ሰብል ውስጥ የሚተከል ነው፡፡
 
የባላፉቺ ግንዱም ሆነ ቅርፊቱ ይላጥና ነጭ ቀለም ይይዛሉ፡፡ የብርሃን (የብሩህነት) ምሳሌ ናቸው፡፡ ግንዱም ከግራር ምሳና ነው የሚዘጋጀው፡፡ ቀደም ብሎ ብዛት ያለው ግንድ እና ባላፉቺ ይቆረጥ ነበር፡፡
 
አንድ ሰው ከ20 እስከ 60 ግንድ ድረስ ይቆርጥ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ አክባሪዎቹ ከማሳቸው አነስተኛ ቁጥር ያለው ግንድ ቆርጠው ያዘጋጃሉ፡፡ የተቆረጠው ግንድ እና ባላፉቺ ከጫካ ወደ ሠፈር የሚጓጓዘው መስከረም 16 ማለትም በመስቀል ዋዜማ ነው፡፡
Image may contain: grass, outdoor and nature
ደመራ በአዊኛ ‹ድሩፂ› ይባላል፡፡ በመስቀል በዓል ሴቶችም ልዩ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ጠላ ይጠምቃሉ (ስልኼ ዜካታና)፡፡
 
ለመስቀል በዓል ‹ወፍ እንኳን በግንድ ቅርፊት ላይ ጠላ ትጠምቃለች› የሚል የአዊዎች አባባል አለ፡፡
 
ሴቶቹ በድርብ እንጀራ ላይ ቅቤ እና በርበሬ በመቀባት ጉዝጉዝ የተባለ ባሕላዊ ምግብ የማዘጋጀት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለዚህ ሥራ አስፈላጊውን ቅመማ ቅመም ቀደም ብለው ይሸማምታሉ፡፡
 
የደመራ ዕለት በርበሬ ይደቆሳል፤ ቅቤም ይነጠራል፡፡ የደመራ ዕለት ምሽት ላይ ከሚከናወኑ ሥነ ስርዓቶች መካከል ሰብል ውስጥ ባላፉቺ መትከል እና እንጀራ እና ጠላ ወስዶ መቀማመስ አንዱ ነው፡፡
 
‹አሪሜኪ አኻ ምርቶኪ ሴጋ ፂፒ ድባን› በማለት ጥቂት አረም በመንቀል ባላፉቺው ላይ ይሰቅሉታል፡፡ ‹አምላክ ሆይ ዓመቱን የምርት አድርግልን፤ አረሙን ወደ ውስጥ ምርቱን ወደላይ አድርግልን› ማለት ነው፡፡
ይህ ሥነ ስርዓት በሁሉም የእህል ዘር ውስጥ ይከናወናል፡፡ ንብ የሚያንብ አርሶ አደር ደግሞ ዘመኑ የማር እንዲሆንለት በመመኘት ድሩፃ እያለ ተመሳሳይ ሥነ ስርዓት ያከናውናል፡፡
Image may contain: plant, tree, grass, outdoor and nature
የደመራ ዕለት የሚከናወነው የመጨረሻው ሥነ-ስርዓት ደጃፉ ላይ ባላፉቺ መትከል እና ምሰሶው ላይ ከአንድ እስር ችቦ ጋር አብሮ ማሰር ነው፡፡ ደጃፍ ላይ የሚተከለው የባላፉቺ ቁጥር ከሦስት በታች አይሆንም፡፡
 
እዚህም ልክ እንደ አዝመራው ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ጠላ እና እንጀራ በአዋዜ ቀርቦ የሚቀመስበት ሥነ ስርዓት አለ፡፡ በዚህ እለት ግንድ እና ባላፉቺ ለማዘጋጀት አቅም ለሌላቸው በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች የቅርብ ዘመዶቻቸው ግንድ እና ባላፉቺ በመውሰድ እንኳን አደረሳችሁ ድሩፃ ማለት የተለመደ ነው፡፡
 
ስጦታ ተቀባዮችም መቶ ሺህ ዓመት ያኑራችሁ (ሊኻ ሻይ አማቶ ታምፓን) ዓመቱን ይድገመን በማለት ይመርቃሉ፡፡
 
ለመስቀል የሚዘጋጀው ጠላ አዲስ ስለሚሆን ‹ሽትቴ ኬሜሳን› በማለት እንዲቀምሱ ይደረጋል፡፡ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ወይም የሰፈሩ ቁጥር በዛ ያለ ከሆነ ቀደም ብለው ካሉት ነዋሪዎች በዕድሜ ትልቅ ከሆኑ አዛውንት ቤት በመጀመር ግንድ ወደ ቤት የማስገባት ሥነ ስርዓት ይካሄዳል፡፡
 
ለሁለት ለሁለት በመሆን ግንድ ወደቤት ይዞ በመግባት ‹እዮሄ እዮሄ እዮሄ ድሩፂ ድሩፃ ድሩፂ ድሩፃ› በማለት ቀድሞ የተዘጋጀ ደረቅ እንጨት ማቀጣጠያ ካለበት ምድጃ እርጥቡ የተላጠ ድፍን ግንድ ‹ኩ ኩ ኩ ኩ ኩ ኩ ኩ› በማለት ቤት ውስጥ ይደምራሉ፡፡
Image may contain: one or more people and fire
ከደጃፍ አንዲት ብቻ ግንድ በመተው ሁሉም መንደርተኛ ተገኝቶ እዮሄ እያለ በእልልታ በደስታ ምድጃውን ከበው ይዘፍናሉ፡፡ በዚህ ሰዓት በቆላማው የአዊ አካባቢ ሳር ቤት ከሆነ ምሰሶ ላይና ከምሰሶ ገበታ ላይ ቅቤ በመለጠፍ ሲቀቡ ይታያል፡፡ አናታቸው ላይም በትንሹ ይቀባሉ፡፡
 
ከዚህ ሥነ ስርዓት ቀጥሎ እናቶች ያዘጋጁትን ጉዝጉዝ ጠላ እና አረቄ ያቀርባሉ፡፡ በዱባ ቅጠል ላይ እየተደረገ ጉዝጉዝ ለታዳሚዎች ይሰጣቸዋል፡፡
በዱባ ቅጠል ላይ ተደርጎ የሚሰጥበት ምክንያት በብዛት ቅቤ ስለሚደረግበት ልብስ እንዳያበላሽ እና ዘመኑ የምርት እና የልምላሜ እንዲሆን በመመኘት ነው፡፡
በየቤቱ በዚህ ሁኔታ እየተዞረ ግንድ የማስገባት ሥነ ስርዓት እየተከናወነ ያመሻል፡፡ አሁን አሁንማ ቆላማ አካባቢ ካልሆነ በስተቀር በቆሎ በደመራው ውስጥ አይበስልም፡፡
 
የስኳር ድንች ዓይነት የበረሃ ድንች ወይም ቡያ ከበቆሎ ጋር ተደባልቆ በግንድ ደመራ ፍም ተጠብሶ ይቀመሳል፡፡
 
ምንም እንኳ ቡያ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ቢበላም የበቆሎ እሸት መጀመሪያ የሚቀመሰው ከመስቀል በዓል በኋላ ነው፡፡ ‹አማማ ይ ሼዋጃይ ይ ኛራጃይ እፄ› የጤና ምግብ ይሁንልን እንደ ማለት ነው፡፡
 
ጥንት ከመስቀል በፊት ወይም በአካባቢው ልማድ ‹መስቀል ሳይሽረው በቆሎም ሆነ አገዳ መብላት ለጉንፋንና ተያያዥ በሽታ ያጋልጣል› ተብሎ ይታመን ነበር፡፡
አሁን ግን ዕድሜ ለመስኖ ልማት ዓመቱን ሙሉ እሸት አለ፡፡ በሽታንም ቀድሞ በመከላከል መቀነስ እየተቻለ ነው፡፡
 
የደመራ ዕለት የአዊ ልጃገረዶች እንሶስላ ይሞቃሉ፤ በነጋታው የመስቀል ዕለት አምረው እና ተውበው አዲስ ልብስ ለብሰው ለመውጣት ይዘጋጃሉ፡፡
 
በመስቀል ወቅት ከልጅ እስከ አዋቂ አዲስ ልብስ መልበስ የተለመደ ነው፡፡ አቅም የሌለው እንኳን አጥቦ የመልበስ ባሕላዊ ግዴታ አለበት፡፡
 
መስከረም 17 የመስቀል ዕለት ማለዳ በመነሳት አዲስ ልብስ ይለበሳል፡፡ ቀደም ብሎ ተሰብስቦ የተዘጋጀውን ችቦ በመያዝ ከደጃፉ ባላፉቺ ወይም ደመራ እንዲያያዝ በማድረግ በአካባቢው ወደሚገኝ ትልቅ ዛፍ ጉዞ ይደረጋል፡፡
ይህ ቦታ በየዓመቱ የመስቀል ማክበሪያም ነው፤ ‹ብራንፂ› ይባላል፡፡ ለምንም አገልግሎት ከዛፉ ላይ መቁረጥ አይፈቀድም፡፡ ዛፉ ዋርካ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡
 
ወደበዓል ማክበሪያው ቦታ ለመሄድ የጥሩምባ እና ‹እዮሄ እዮሄ እዮሄ› የሚል ድምፅ ከየአቅጣጫው ይስተጋባል፡፡
 
የደመራ ዕለት አንዳንዴ በየቤቱ በመዞር እና በመጠጥ ድካም ከባድ እንቅልፍ የጣለው ሰው በድምፁ እና በሚስተጋባው ዜማ በመባነን ይነሳል፡፡
 
በዕለቱ ምድጃ ላይ እሳት ማሳደር ግዴታ በመሆኑ መጫሪያ ይዞ እሳት ወይም ፍም ልመና መውጣት ነውር ነው፡፡ ፍሙን አመድ ውስጥ አዳፍኖ ማሳደር ይበጃል እንጂ፡፡
 
የመስቀል ዕለት አብዛኛዎቹ እናቶች ቀደም ብለው ተነስተው ምጣድ ይጥዳሉ፡፡ አዋዜ እና ቅቤ አገናኝተው ጉዝጉዝ ያዘጋጃሉ፡፡ ምጣድ ላለመጣድ ያቀደች እናት ከደመራ ዕለት በፊት ያልተቀባ እንጀራ አሳድራ ቅቤ እና አዋዜ አገናኝታ ታዘጋጃለች፡፡
 
ጠላ እና ጉዝጉዝ የተሸከሙ ሴቶች ችቦ የያዙ ወንዶችን ተከትለው ወደ ማክበሪያው ሥፍራ ይጓዛሉ፡፡ የመንደሩ ሰው በተቻለ መጠን ተጠባብቆ በአንድነት እና በጋራ ሆኖ በድምቀት ‹እዮሄ ድሩፃ› እያለ ከቦታው ይደርሳል፡፡
የጋራ ማክበሪያው ስፍራ ላይ የአካባቢው ትልቅ ሰው ወይም ተረኛው በደመራ ዕለት አንዲት መጠነኛ ባላፉቺ ይተክላል ወይም ይደምራል፡፡ ችቦውን የያዙ ነዋሪዎች ሦስት ጊዜ ደመራውን ከዞሩ በኋላ በሁለት ረድፍ እኩል ተከፍለው ይቆማሉ፡፡
Image may contain: food
አቋቋማቸው ግማሾቹ ወደ ሰሜን ግማሾቹ ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመሆን በምሥራቅ እና በምዕራብ በኩል ያለውን ክፍት ይተውታል፡፡
 
በመቀጠልም ሦስት በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ይመርቃሉ፡፡ ምርቃቱ እንደ ተጠናቀቀ ‹ድሩፃ ድሩፃ ድሩፃ› በማለት ሁሉም በአንድ ጊዜ ችቦውን ወደ ደመራው ይወረውሩታል፡፡
 
በዚህ ሰዓት ሕጻናት እኩል መወርወር እና እስከደመራው ማድረስ ስለማይችሉ ‹አይዞህ አድርሰህ ድሩፃ በል› ይባላሉ፡፡
 
በነገራችን ላይ ችቦ የሚይዝ ወንድ ብቻ ነው፡፡ አቅም የሌለው ታሞ አልጋ ላይ የተኛ ሕጻንና በሕይወት የሌለ የቤተሰብ አባል በስሙ ሁለተኛ ችቦ ይወጣለታል፡፡ በተለይ በሞት ለተለየ የቤተሰብ አባል ለብዙ ጊዜ ችቦ እንዲወጣለት ይደረጋል፡፡
ችቦው ደመራው ላይ ከተለኮሰ በኋላ ልክ በግንድ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደሚደረገው ሁሉ ጉዝጉዝ፣ ጠላ፣ አረቄ፣ እሸት በቆሎ ቀርቦ ይበላል ይጠጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የበዓሉ አክባሪዎች ቁጥር ብዙ ከሆነ በሬ ወይም ላም፣ ጥቂት ከሆኑ በግ ወይም ፍየል ይታረዳል፡፡ ስጋውም እዚያው ተሰርቶ ይበላል፡፡ ዕለቱ ፆም ከሆነ ግን በሽሮ የተዘጋጀ ‹አብዚ› የተባለ ምግብ ነው የሚቀርበው፡፡
 
በነጋታው ሰብሰብ ብለው እርዱን ይፈፅማሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ችቦ ይዞ የመውጣት ሥነ-ስርዓት ከጥዋት ይልቅ ከሰዓት በኋላ የሚከናወንበት ሁኔታ አለ፡፡ የዚህ ዓይነት ስርዓት ዚገም ወረዳ ጎደር ጃዊ አካባቢ ይፈጸማል፡፡
Image may contain: plant, flower and food
በተለይ እዚህ አካባቢ ነዋሪዎቹ በጥዋት ተነስተው ችቦ ከባለፉቺ ጋር እንጀራ በአዋዜ እና እንዲሁም ጠላ ይዘው ወደ ከብቶች ማደሪያ (በረት)ይሄዳሉ፡፡ ሌላው የተለመደው ነገር በዚህ ወቅት ለከብቶች አሞሌ ጨው መስጠት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ ወተት እና ቅቤ የሚትረፈረፍበት ወቅት እንደሆነ ይወሳል፡፡ አሁን ግን መቀነሱ ይነገራል፡፡
 
የመስቀል በዓል በአዊ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዚህ የበዓል ወቅት የመስቀል ጠላ ጠጡ እየተባለ ይጠራል፡፡
 
በተለይ በፋሲካ የተጋቡ አዳዲስ ጥንዶች የመስቀል ልዩ ጉዝጉዝ እና ጠላ ተደግሶላቸው ይጠራሉ፡፡ መስቀል ወንዞች ከሙላታቸው ቀንሰው እና ጎድለው ሰው ከዘመድ ጋር የሚጠያየቅበት ወቅት ነው፡፡
 
አርሶ አደሩም ከክረምት ሥራው ተላቅቆ የተወሰነ እረፍት የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ የመስቀል በዓል በተለዬ ሁኔታ በአዊ ይከበራል፡፡
ድሩፃን፤ ሊኻ ሻይ አማቶ ታምፓን!
 
ዘጋቢ፡- አይሸሽም አባተ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here