“የሚያባሉን ሰዎች እድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች ናቸው፤ ወጣቱ መንቃት አለበት፡፡” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር)

0
48

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን አለመግባባት ከሕዝቡ ጋር በማስተሳሰር ሕዝብ እንደተጋጨ ተደርጎ የሚወሰደው እሳቤ መስተካከል እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል፡፡ በመደበኛ ስብሰባው ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የሀገሪቱ ሰላምና የዜጎች ደኅንነት ይገኙበታል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ካነሷቸው እና ምላሽ ከተሰጠባቸው ነጥቦች መካከል ከለውጡ ማግስት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች እየተስተዋሉ በመሆኑ የዜጎች የተረጋጋ ህይዎት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ በክልል መሪዎች መካከል የሚታየው የቃላት ልውውጥ፣ በፌደራል መንግስት ስር የሚተዳደሩ ክልልን ከክልል የሚያገናኙ መንገዶች የመዘጋት ጉዳይ፣ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንቅፋት እየገጠመው መሆኑ እና የሀገሪቱን ሕዝብ አንድነት የሚሸረሽሩ ፀብ አጫሪ ንግግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸው ይገኙበታል፡፡ ከማንነትና ከራስ አስተዳድር ጥቄዎች ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል የሚነሱ ጥያቄዎች ለምን እልባት እንዳልተሰጣቸውም ተጠይቋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) በሰጡት ማብራሪያ “የውጊያ ቀስቃሾቹ ሁል ጊዜም አንድ አይነት ሰዎች ናቸው፤ ግጭት እየቀሰቀሱ እነሱ ወጣት ማስገደል እንጅ መሞት አያውቁበትም፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ተገንዝቦ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ሲሉ መክረዋል፡፡ “የሚያባሉን ሰዎች እድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች ናቸው፤ ወጣቱ መንቃት አለበት፤ እነሱን እያደመጠ ወደ ግጭት መግባት የሌለበትም ” በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ወጣቱ እንደዚህ አይነት ሰዎችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማንቃት፣ ሕዝቡም በጦርነት ለውጥ እንደማይመጣ ተገንዝቦ መፍትሄ ማስቀመጥ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን አለመግባባት ከሕዝቡ ጋር በማስተሳሰር ሕዝብ እንደተጋጨ ተደርጎ የሚወሰደው እሳቤ መስተካከል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች የቆየ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ በአማራ ክልል ከቅማንት የራስ አስተዳድርና የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም ሲያብራሩም የአማራና የቅማንት ሕዝብ የማይነጣጠሉ፣ ከማንም በላይ አንዳቸው ለአንዳቸው ቅርብ፣ አንድ አይነት ሕዝብ ናቸው መሆናቸውን ለምክር ቤት አባላቱ አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ለተነሳው የቅማንት ጥያቄ መልስ መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡ የግጭት መንስኤ ተደርገው እየተወሰዱ ያሉት ሦስት ቀበሌዎች እንደሆኑ፣ጥያቄዎቹ መልስ እንዲያገኙም በሰላም ከመፍታት ይልቅ የሰው ህይዎት መጥፋት እንደሌለበት ሕዝቡ ማጤን እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ በነዚህ ቀበሌዎች ጥያቄ ምክንያት ሕዝብ እያጋጩ ያሉ ግለሰቦች እንዳሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል መንግስትም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡ ሰው በሰላማዊ መንገድ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ መንገድ ሲዘጉ የነበሩ አካላት መኖራቸውንም ጠቅሰው በየትኛውም አካባቢ መንገድ መዝጋት ይቅርና ድንበር መዝጋት በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል፡፡ መንስኤው የኋላ ቀር የፖለቲካ አስራር ውጤት በመሆኑ መንግስት ከሕዝቡ ጎን በመሆን ችግሮችን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here