የሠላም ጉዳይ በመንግሥት ብቻ የሚረጋገጥ ባላመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አሳሰቡ፡፡

0
37

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 26/2012ዓ.ም (አብመድ) በደብረ ታቦር የሠላምና የዴሞክራሲ ውይይት እየተካሄደ ነው። የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች፣ የዞኑ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ከደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በደብረ ታቦር እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶክተር) እንደተናገሩት ወጣቱ በፕሮፖጋንዳ እየተነዳ ለኢትዮጵያ ፈተና እየሆነ ነው፤ በሀገሪቱ ሠላም ለማስፈንም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል፡፡

‹‹ሠላም እንዲሰፍን የሥነ ምግባር አስተምህሮ እና ውይይት ያስፈልጋል። ስለዚህ በትምህርት ቤቶች እና በሃይማኖት ተቋማት በኩል የሥነ ምግባር ትምህርት ሊሰጥ ይገባል›› ያሉት ዶክተር ዳኛቸው እያንዳንዱ ማኅበረሰብ እራሱን መፈተሽ እንዳለበትም አሳስበዋል። የሠላም ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም በየድርሻው ስለሠላም መወያዬት እንዳለበትም አስረድተዋል።

‹‹በአንድ ሀገር ውስጥ የአመለካከት ልዩነት መኖር ችግር የለውም›› ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ችግር የሚሆነውን ተወያይቶ በሠላም መፍታት አለመቻል እንደሆነም አመልክተዋ።

ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን የመሪዎችና የተቋማት ፍላጎት እና ባሕል ወሳኝ እንደሆኑ ጠቁመው ለፖለቲካ እና ለሃይማኖት ሽፋን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ማጣላት እንደማይገባም ገልፀዋል።

በግለሰቦች የሚታየው አለመረጋጋት ለሌላው ማኅብረሰብ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ በዘረኝነት፣ በጎጥ እና በአጀንዳ የንሚነዱ አሉባልታዎች ቆም ብሎ መፈተሽ እንደሚገባም መክረዋል።

ዘጋቢ፡- አማረ ሊቁ -ከደብረ ታቦር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here