የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ፡፡

0
13
ባሕር ዳር፡ መስከረም 06/2013ዓ.ም (አብመድ) የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የሁለተኛ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈጻጸም ስኬትና ፈተናዎች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ አስር ዓመት (2013 እስከ 2022) ዕቅድ ግብዓት የሚሰጥ የባለድርሻ አካላት ምክክር ትናንት በአዳማ መካሄዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
በምክክር መድረኩ ከእርሻ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ዳይሬክቶሬት እና ከሀገር አቀፍ የባለሀብቶች ማኅበር በኩል በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት የልማት እንቅስቃሴ የተገኙ ስኬቶችና ልማቱ በዕቅዱ መሠረት ተሠርቶ ለአገር ኢኮኖሚ ተገቢ አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት የሚያመላክት ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
 
በውይይቱ ወቅት የሰፋፊ እርሻ ኢንቨሰትመንት በዕቅዱ መሠረት እንዳይሠራ ማነቆ የሆኑ ችግሮችም የግብዓት አቅርቦት፣ በቂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመኖር፣ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነትና ፍትሐዊነት ችግር፣ የሚሠራና የማይሠራ ባለሀብትን ለይቶ ድጋፍ አለመስጠት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች መከሰት ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ ተነስቷል፡፡
 
በውይይቱም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በቅንጅትና በተናበበ መልኩ በመሥራትና ክትትልና ድጋፊ በማጠናከር እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት በዕቅዱ መሠረት እንዲሠራ ለማድረግ ርብርብ ሊደረጉ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
 
በምክክር መድረኩ የተገኘው ‘ጂ አይ ዜድ’ የተባለው የጀርመን ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ድርጅቱ የኢትዮጵያን የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ልማት እንዲጠናከር የመንግሥትንም ሆነ የግል ባለሀብቶች አቅም ለማሳደግ በተቋማት አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ አቅርቦት ለመደገፍና ለማብቃት እና በፖሊሲ ዝግጅት ለማገዝ መዘጋጀቱንና ፕሮግራሙን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቅርቡ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
 
በምክክር መድረኩ የግብርና ሚኒስቴር የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች የግብርና፣ የኢንቨስትመንትና የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የግብርና ምርምር ኃላፊዎች፣ የልማት ባንክ ተወካዮች እና የልማት ደጋፊ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
 
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶክተር) በውይይቱ የተነሱ አብዛኞቹ ጉዳዮች በዘርፉ የለውጥ ማሻሻያ እየታዩ ያሉ ጉዳዮች ስለሆኑ ማሻሻያው ሲጠናቀቅ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ተጨማሪ ግብዓት በመውሰድ የጋራ ሰነድ ሆኖ ማነቆዎችን የሚፈታ የፖሊሲ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል እየተሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here