የብልፅግና ፓርቲ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን እንዲፈታ ሆኖ የተቀረፀ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

0
119

የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ኃላፊዎች በብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም ዙሪያ ምክክር እያደረጉ ነው።

በአዲሱን የውሕድ ፓርቲ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ዙሪያ በተመለከተ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ መካከለኛ የሥራ ኃላፊዎች ምክክር እያደረጉ ነው።

በምክክሩ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ለአብመድ እንደገለፁት የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ሕዝቦችን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ይዟል። የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም ገና ያላለቀ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ <<የብልፅግና ፓርቲ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ያካተተ ነው>> ብለዋል። ኢሕዴግን ወደ ውሕድ ፓርቲ ለማምጣት ከዚህ በፊት በምሁራን ጥናት እንደተደረገ የገለፁት ተሳታፊዎቹ በተደረሰው የጥናት ውጤት ላይ የኢሕአዴግ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች የበሰለ ውይይት አድርገውበት ከግንባርነት ወደ ውሕድነት እንዲመጣ ወስነዋል ነው ያሉት። በአማራ ክልልም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በውሕድ ፓርቲው ዙሪያ ተዳጋጋሚ ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።

የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በሚመክሩበት የብልፅግና ፓርቲ ውይይት በውሕድ ፓርቲው ያልተካተቱ ጉዳዮች እየተነሱ እንደሆነና ግልፅ ያልሆነው ጉዳዮች ማብራሪያ እየተሰጠበት መሆኑን
ነው የተናገሩት። የውሕድ ፓርቲው ፕሮግራም ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ደረጃ የሚመጥን ነው ያሉት ተወያያዎቹ የክልሉንና የሀገሪቱን ጥያቄዎች የመመለስ አቅም እንዳለውም ገልፀዋል። ውሕድ ፓርቲው እስካሁን ሀገሪቱ የመጣችበትን የፖለቲካ ቅኝት በማስተካከል ኅበረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያስችላልም ነው ያሉት። ውሕደቱ የጠቅላይነት ሐሳብን ያራምዳል የሚባለውም ፈፅሞ የተሳሳተ እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው የውይይቱ ዓላማ የአዲሱ ፓርቲ ሕገ ደንብና ፕሮግራም ላይ በመወያዬት ግብዓት መሰብሰብና ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮችን ማብራሪያ በመስጠት ወደሕዝቡ እንዲወርዱ ማድረግ ነው ብለዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ በንግግራቸው አዲሱ ፓርቲ የአማራን ሕዝብ የማንነት፣ የድንበር እና ሌሎች ጥያቄዎችን እንዲፈታ የጋራ መግባባት እንዳለበትም ገልፀዋል። ፓርቲው የማንነትና የድንበር ጥያቄዎችን እንዲፈታ ሆኖ የተቀረፀ እንደሆነም ገልፀዋል። የሕዝቡ ጥያቄም ቀስ በቀስ እንደሚፈታ ነው የገለፁት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የአፈጻጸም ችግሮች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ ፓርቲ ብሔርን ሳይረሳ ሀገርንም የያዘ ነው ብለዋል። አዲሱ ፓርቲ በውይይት የተመሠረተ፣ በውይይት የሚያምን ሁሉንም ብሔሮች የሚያሳትፍ እንጂ ጠቅላይነት አንደሌለው ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ መፈጠር ብቻ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ እንደማይሆን ያነሱት ርዕሰ መስተዳደሩ ለችግሮች መፍትሔ የሚሆነው በተቀመጠው ሕግና ደንብ መምራትና መፈፀም ነውም ብለዋል። ውሕድ ፓርቲው እስካሁን የነበረውን የፓርቲ መርህ ጥሰት እንደሚያስቀርም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here