የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበረሃ አንበጣ ምክንያት ርሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡

0
46
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ እና ሶማሊያ የበረሃ አንበጣ እያደረሰ ያለው ጉዳት ርሃብ እንዳያስከትል ስጋቱን ገልጧል፡፡
 
በድርጅቱ የምግብና እርሻ ድርጅት የአደጋ ምላሽ ተጠሪ ዶሚኒክ በርገን እንዳስታወቁት በምሥራቅ አፍሪካ እየተከሰተ ያለው የበረሃ አንበጣ መስፋፋት ካልተገታ ሰብልና የእንስሳት መኖን በማውደም የርሃብ አደጋ በቀጣናው ሊያስከትል ይችላል፡፡
 
ከዚህ ቀደም የተደረገው የበረሃ አንበጣውን የመቆጣጠር ሂደት ስኬታማ አለመሆኑን ያመላከተው ተመድ በአውሮፕላን ኬሚካል መርጨት ውጤታማው የመከላከያ ዘዴ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ያጋጠማቸው ሀገራት ለዚህ በቂ ግብዓት እንደሌላቸው ነው የገለጸው፡፡ ይህም የመከላከሉን ሥራ ውጤታማነት አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ርሃብ ሊከሰት ይችላል የሚለው ስጋትም ከዚህ ጋር የተገናኘ ነው፡፡
 
በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር የበረሃ አንበጣ የያዘው መንጋው የበለጠ እራሱን እንዳያባዛም አስግቷል፡፡ እንደ ትንበያው በፍጥነት የሚራባው የበረሃ አንበጣ እስከ መጭው ሰኔ እራሱን እስከ 500 እጥፍ ሊያባዛ ይችላል፡፡
 
ስጋቱን ተከትሎም ተመድ የበረሃ አንበጣ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ለማድረግ የሚያግዝ ወደ 76 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ከለጋሽ አካላት ጠይቋል፡፡ ይህ ድጋፍ ተገኝቶ ወደ ርጭት ተገብቶ መቆጣጠር ካልተቻለ ግን ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል ርሃብ በአካባቢው ሊመጣ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
 
የበረሃ አንበጣው ስርጭት በኬንያ በ70 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማያውቅ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያውም በ25 ዓመታት ውስጥ ያልታዬ እንደሆነ ነው ተመድ የገለጸው፡፡ ሶማሊያ የበረሃ አንበጣውን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አውጃለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በአራት ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ አስመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ እየገለጸ ነው፡፡ መንጋውን ለመከላከል የድጋፍ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡ ኬንያም በአውሮፕላን ርጭት እያካሄደች ነው፡፡ ዩጋንዳ በሰሜናዊ ግዛቷ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ወታደሮቿን ለማሰማራት እየተሰናዳች ነው፡፡
 
የበረሃ አንበጣው ከሦስት ወራት በፊት ከየመን አካባቢ እንደተነሳ ታውቋል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here