የተባበሩት የአማራ በጎ አድራጎት ድርጅት ተመሠረተ።

0
21

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) በሰዉ ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ አማራዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የተባበሩት የአማራ በጎ አድራጎት ድርጀት ተመሠረተ፡፡

በጎ አድራጎት ድርጀቱ በአማራ ክልል እና ከክልሉ ውጭ ያሉ አማራዎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዳይጣሱ ከመታገልም ባለፈ አኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅማቸዉ እንዲከበር ይሠራልም ተብሏል።

ማኅበሩ “በትናንት ላይ ተመሥረተን ነገን እንሠራለን” በሚል መሪ ሐሳብ የመጀመሪያ የምሥረታ ጉባኤዉን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ በጉባኤዉም የማኅበሩ የምሥረታ ዓላማ እና አጠቃለይ ገጽታ ቀርቧል፡፡

የማኅበሩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶክተር) እንደተናገሩት የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ሀገረ መንግሥት በመመሥረት እና ታሪክን ጠብቆ ለትዉልድ በማስረከብ በኩል የተሻለ አስተዋጽኦ አበርክቶ እያለ ታሪኩን በማጠልሸት ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጥ ቆይቷል፡፡ይሁን እንጅ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ አማራዎችን በተደራጀ መንገድ የሚረዳ አካል እስካሁን አልነበረም፤ እናም ማኅበሩ ይሄን ክፍተት እንደሚሞላ እምነታቸዉን ገልጸዋል፡፡

የአደራጅ ኮሚቴዉ ምክትል ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አዉግቸዉ ደግሞ “በአማራ ክልል ውስጥ የክልሉን ልማት የሚያፋጥኑ እና ችግሮችን ለመፍታት የሚሠሩ ድርጅቶች ቢኖሩም ከክልሉ ውጭ ያሉ አማራዎችንም ችግር ትኩረት የሚሰጥ ድርጅት አስፈላጊ ነው”ሲሉ የማኅበሩን ምሥረታ ተገቢነት አስረድተዋል።

በምሥረታ ጉባኤዉ የተገኙት የአማራ ክልል በይነ መንግሥታት ቢሮ ኃላፊ ደስታ አስፋዉ (ዶክተር) ማኅበሩ የአማራ ተወላጆችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረዊ ችግሮች ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት የማገዝ ተስፋ እንዳለዉ ገልጸው ሁሉም ማኅበሩን በማጠናከር በኩል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎችም የማኅበሩን ምሥረታ አስፈላጊነትና ለውጤታማነቱም እንደሚሠሩ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ -ከአዲስ አበባ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here