“የአማራ ሕዝብ የትግራይ ወንድምና እህቶቹን ይቅርና ድንበር አቋርጠው የሚመጡትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ነው፡፡” ኤርትራውያን ተማሪዎች

0
102

የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ እና አቃፊ መሆኑን ከትግራይ ክልል የመጡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናግረዋል::

ህይዎት ሀለፎምና ትርሀስ ገብረ እግዚአብሄር የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው እና በአካባቢው በነበራቸው ቆይታ ምንም የደኅንነት ስጋት እንዳላጋጠማቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ለተግባር ልምምድ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንደነበር የተናገሩት ተማሪዎቹ በቆይታቸው የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ እና እንግዳ ተቀባይ መሆኑን እንደታዘቡ ነው ያረጋገጡት፡፡

ከኤርትራ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ሔርሞን ገዛኢ እና ክብሮም አክሊሉ በእነ ህይዎት ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን አቃፊ ነው፤ ከሕዝቡ የስነልቦና ውቅር ውጪ የሚሰራጨው የተሳሳተ ትርክት ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል መንግስት ‘በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን አልልክም’ ሲል ያወጣው አቋም ከነባራዊ እውነታው ጋር የሚጋጭ እና በሕዝቦች አብሮነት ላይ የተሳሳተ ስጋት የሚፈጥር እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

እውነታው የአማራ ሕዝብ የትግራይ ወንድምና እህቶቹን ይቅርና ድንበር አቋርጠው የሚመጡትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ሆኖ እያለ ተማሪዎች ወደ ሌላኛው የሀገራቸው ክፍል ሄደው እንዳይማሩ ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገቢነት እንደሌለውም አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አህመድ ሞሀመድ “ከመላ ሀገሪቱ የተመደቡ አዲስ እና ነባር ተማሪዎችን ተቀብለን እያስተናገድን ነው” ብለዋል፡፡ በትምህርት ዘመኑ ከትግራይ ክልል 45 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መዝግበው እያስተማሩ እንደሆነም ነው አቶ አህመድ ለአብመድ የገለጹት፡፡

ይህም የአማራን ሕዝብ ተቻችሎ የመኖር እሴት ጥላሽት ለመቀባት የሚደረገው ሙከራ ፍሬ አለማፍራቱን ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ወደ ዩኒቨርሲቲው ልጆቻቸውን የላኩ የትግራይም ይሁን የሌሎች አካባቢ ወላጆች ስጋት ውስጥ እንዳይገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here