የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የወልዲያ ከተማ የአስፓልት መንገድ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ሰጡ፡፡

0
43

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወልዲያ ከተማ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ግንባታን እና የሼህ ሁሴን ሙሀመድ አሊ አል ሙዲን ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡

አቶ ተመስገን የከተማው አስፓልት መንገድ በተያዘለት ዕቅድ ልክ እየተሠራ ያልሆነው የከተማ አስተዳድሩ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የካሳ ጉዳይ በወቅቱ አለማጠናቀቃቸው ነው ለተባለው ምክንያት ሁለቱንም ወገኖች አገናኝተዋል፡፡ የሁለቱ ወገኖች ተወካይ እና በወልዲያ ከተማ ጠንካራ ኮሚቴ በማቋቋምም የካሳ ጉዳይ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቅቆ ሥራው በሙሉ አቅም እንዲገነባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ሕዝቡ በየጎዳናው በተቆፈረው የመሠረተ ልማት ምክንያት የከፋ ችግር እንዳይገጥመውና የንግድ እንቅስቃሴው እንዳይገታ ከተማ አስተዳድሩ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል በክልል ደረጃ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

‹‹ተጨማሪ ልማቶችን ለመጠየቅ የተጀመረውን ማጠናቀቅ ያስፈልጋል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የከተማው መንገድ ከክረምት በፊት መጠናቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሼህ ሁሴን ሙሀመድ አሊ አል ሙዲን ዓለም አቀፍ ስታዲየም የከተማዋ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ስታዲየሙ ዙሪያ ያሉ ማዕከላት ለንግድ ሥራ እንዲውሉ ለማስቻል የማስተዳደር ኃላፊነቱን በአጭር ጊዜ አቅርበው እንደሚወስኑ ተናግረዋል፡፡ አቶ ተመስገን በከተማዋ ‹‹አሁንም ስታዲየሙን የሚመጥኑ ሆቴሎች እንዲገነቡ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ ሆቴሎች እንደገና እንዲሠሩ የከተማዋ የልማት ኮሚቴ ሊሠራ ይገባል›› ብለዋል፡፡

የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ እንደቀድሞ ለማፋጠን ከልማት ኮሚቴው በላይ በሆኑ ጉዳዮች ክልሉ በቅርበት እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ‹‹በወልዲያ ከተማ የሚሠራው 5 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ከሦስት ወራት በኋላ ሊጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ የነበረና የተጓተተ ፕሮጀክት ነው›› ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ መጓተት የወሰን ማስከበር ችግሮች በከተማ አስተዳድሩ፣ በባለስልጣኑ በኩል እንደነበርና የፀጥታ ችግርም በተፈለገው ልክ እንዳይሠሩ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር በመሆን አቅጣጨ በመሰጠቱ በሁለት ሳምንታት የወሰን ጉዳይ ተጠናቅቆ እስከ ዛሬ ስድስት ወር ድረስ ዋና ዋና የመንገዱን ክፍሎች ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ኢንጂነር ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የትኛውም ምክንያት የከተማዋን የመንገድ ፕሮጀክት እንዳያዘገየው የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች በኃላፊነት እና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከወልዲያ ባሕር ዳር ድረስ ያለው የአስፓልት መንገድም ጥገና መጀመሩን ኢንጂነር ሀብታሙ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ -ከወልዲያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here