የአማራ ክልል የቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት በበጀት ዓመቱ 40 ሚሊዮን ብር ሰብስቦ ለቅርስ ጥበቃና ልማት ለማዋል እየሠራ ነው፡፡

0
98

የቱሪስት መዳረሻዎች የክልሉ አማራጭ የገቢ አርዕስቶች እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ የሽዋስ ደሳለኝ ለአብመድ እንደተናገሩት የቱሪስት መዳረሻዎችንና ታሪካዊ ቅርሶች የክልሉ እድገት አማራጭ የገቢ አርዕስቶች እንዲሆኑ የመሠረተ ልማት ማሟላትና የቅርስ ጥገና ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

እንደ አቶ የሽዋስ ገለፃ በአማራ ክልል የሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፡፡ ቅርሶች ላይ የተደቀነው አደጋ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑም ጽሕፈት ቤቱ የማኅበረሰብ አቀፍ የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

 

በበጀት ዓመቱ 40 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር፤ እስከተያዘው ወር ድረስ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ገንዘቡ በክልሉ ከሚገኙ መዳረሻዎች ከተገኙ የገቢ አርዕስቶችና ዓላማውን ለመደገፍ በኢትዮ-ቴሌኮም በተዘረጋው አጭር የጽሑፍ መልዕክት መቀበያ የተሰበሰበ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በተሰበሰበው ገንዘብም በጭስ ዓባይ ፋፋቴ የመዳረሻ ቦታዎችን የማልማት፣ በጎንደር አብያተ መንግሥታትና በደሴ ሙዚየም የጥገና ተግባራትን ለማከናወን የግንባታ መነሻ በጀት ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ጎብኝዎች ደረጃውን የጠበቀ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ በጭስ ዓባይ ፋፋቴ ግንባታና የእንግዶች ማረፊያ ቤት ጥገና እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻዎችንና ታሪካዊ ቅርሶች የክልሉ እድገት አማራችጭ የገቢ አርዕስቶች እንዲሆኑም ማኅበረሰቡን ያሳተፉ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት፡፡

 

ተቋሙ በቀሪ ወራት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማድረግና ሕዝባዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር በማካሄድ ተጨማሪ ገንዘብ አቅም ለመፍጠር እንደሚሠራም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

የቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ የግል ድርጅቶች ከዘርፉ የሚያገኙት ገቢ መጠን እንደተጠናና ከየካቲት ወር ጀምሮ ለቅርሶች ጥገናና ለመዳረሻ ቦታዎች መሠረተ ልማት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአማራ ክልል ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት የመዳረሻ ቦታዎችን ለማልማትና ቅርሶችን መልሶ ለመጠገን በ2011 ዓ.ም ነበር ወደ ተግባር የገባው፡፡

 

ዘጋቢ፡ ኃይሉ ማሞ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here