የአማራ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በስድስት ወራት ውስጥ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሰበሰበ፡፡

0
21

የአማራ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በ2012 የበጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ከመደበኛ እና ከከተማ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዩን ብር በላይ መሰብሰብ ችሏል፡፡

ከዓመታዊ ዕቅዱ 47 በመቶውን የሰበሰበው የገቢዎች ቢሮ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲነፃፃር በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የባለስልጣኑ የገቢ ዕቅድ እና ጥናት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አትንኩት በላይ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ እቅዱ ላለመሳካቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ የማይቆርጡት ላይ እርምጃ አለመወሰዱ፣ ሀሰተኛ ደረሰኞችን አለመከላከልና እርምጃ አለመወሰዱ፣ ውዝፍ ግብር በማይከፍሉት ላይ እርምጃ አለመወሰዱ እና የግብር ይግባኝ ኮሚቴዎች የሦስተኛ ወገን ውሳኔ በወቅቱ አለማሳወቃቸው ምክንያት መሆናቸውን አቶ አትንኩት ተናግረዋል፡፡

የተገኘው ገቢ የተሰበሰበውም የጠራ ዕቅድ አዘጋጅቶ መግባባት ላይ መደረሱ፣ ከክልል እስከ ወረዳ የተለያዩ የምክክር እና የማበረታቻ ሽልማት መርሐ ግብሮች በመዘጋጀታቸው፣ 97 በመቶ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በወቅቱ በመክፈላቸው የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

በግብር አከፋፈል ደረጃ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን ሰዋ፣ የምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም እና የደቡብ ወሎ ዞኖች ግንባር ቀደሞች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡  ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ደሴ እና ጎንደር ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው እንደሆኑ አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሦድስት ወራት በድክመቶች እና በከፍተኛ ገቢ በሚሰበሰብባቸው ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዕቅዱን ለማሳካት ባለስልጣኑ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ተገልፆል፡፡

ባለስልጣኑ ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 13/2012 ዓ.ም ድረስ ከወረዳዎች፣ ከከተሞች፣ ከ3 ሜትሮፖሊታን ከተሞች እና ከ12 የዞን ተወካዮች ጋር በባሕር ዳር ከተማ የ6 ወራት የሥራ አፈፃፃም ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here