የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ እያቋረጡ ነው፡፡

0
62

ባሕር ዳር፡- ጥር 22/2012ዓ.ም (አብመድ) ኮሮና ቫይረስን በመሥጋት የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን እያሳዎቁ ነው፡፡

ወደ ቻይና እና ከቻይና ወደ ሀገራቸው የሚደረጉ በረራዎችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በጊዜዊነት ካቋረጡት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሮኮ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሽየስ ይገኙበታል፡፡ የኬንያ እና የሩዋንዳ አየር መንገዶች ሁሉም ወደ ቻይና እና ከቻይና ወደ ሀገራቸው የሚደረጉ የበረራ መርሃ ግብሮች እንዲቋረጡ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡ የሞሮኮ አየር መንገድ ደግሞ ወደ ቤጂንግ የሚደረገው ጉዞ ስለቀነሰ እስከ አውሮፓውያኑ የካቲት 29/2020 መገባደጃ ድረስ በጊዜያዊነት በረራ ማቋረጡን አስታውቋል፡፡

የማዳጋስካር አየር መንገድ በከፊል ነው የበረራ መርሃ ግብሩን ማቋረጡን ያስታወቀው፡፡ ወደ ቻይናዋ ጉዋንግዙና ከጉዋንግዙ በመነሳት ወደ ማዳጋስካር የሚደረጉ የበረራ መርሃ ግብሮቹ በጊዜያዊነት እንዲቋረጡ ነው አየር መንገዱ የወሰነው፡፡ ውሳኔውም ከአውሮፓውያኑ የካቲት 1/2020 እስከ መጋቢት 1/ 2020 የሚዘልቅ ነው፡፡ የሞሪሺየስ አየር መንገድም የበረራ መርሃ ግብሮቻቸውን በከፊል ለማቋረጥ ከወሰኑት የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች አንዱ ነው፡፡

አየር መንገዱ ከአውሮፓውያኑ ጥር 31/2020 ጀምሮ ከሻንሃይ በመነሳት ወደ ሞሪሽየስ እና ከሞሪሽየስ ወደ ሻንሃይ የሚደረጉ በረራዎቹን በጊዜያዊነት ማቋረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ ወደ ሆንግ ኮንግ የሚደረገው በረራ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ጥር 22/2012 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገው የበረራ መርሃ ግብር አላቋረጠም፡፡ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ ወደ አምስት የቻይና ከተሞች ማለትም ወደ ቤጂንግ፣ ሻንሃይ፣ ጓንዡ፣ ቼንጉ እና ሆንግ ኮንግ በረራውን በማድረግ ላይ መሆኑን አየር መንገዱ ትናንት መግለጹ ይታወሳል፡፡

በሽታው በብዙ ሀገራት እየተዛመተ በመምጣቱ ኮሮና ቫይረስ የዓለም የጤና ሥጋት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አውጇል፡፡ ገዳዩ ኮሮና ቫይረስ በ21 ሀገራት እንደተከሰተ፤ ቫይረሱ ከ200 በላይ ቻይናውያንን ለህልፈት ዳርጓል፤ በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ 8 ሽህ አሻቅቧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 98 ሰዎች ብቻ ናቸው የሌላ ሀገር ዜጎች፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ቻይናውያን ናቸው፡፡ ከቻይናውን ውጭ ግን ሕይዎቱ ያለፈ የውጭ ሀገር ዜጋ የለም ነው ያለው ድርጅቱ፡፡

ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን እና የዓለም የጤና ድርጅት

በኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here