‹‹የእኛ ፊልሞች ኅብረተሰቡን ሳይሆን ሠሪዎችን ነው የሚመስሉት፡፡››

0
79

‹‹እሴቶችን ያደበዘዙ፤ ዘመን የማይሻገሩ ፊልሞች እንዲበራከቱ የመንግሥት ቸልተኝነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል›› የፊልም መምህር

ቀለም አልባው የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪው ‹‹አሉኝ›› ያላቸውን የጥበብ ውጤቶች ሲለቅ ተመልካቹ ሲተች እና ሲደግፍ ደብዛዛ ጉዞው በሽሙጥ እና በድጋፍ ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ተመልካቾች ገሚሱ የኢትዮጵያውያን ፊልም በመሆኑ ብቻ ለማበረታታት ሲጥር ገሚሱ ደግሞ ብዙ ተከታትሎ በመሰልቸት ‹‹የኢትዮጵያን ፊልም አላይም›› የሚሉ ሐሳቦች ሲንጸባረቁ ከግለሰቦችም አልፎ በፊልሞች ጭምር ሲንጸባረቅ ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያን ፊልም መቀየር የሀገርን ታሪክ እንደማደስ ያለ ነው፡፡

በአብመድ የፌስቡክ ገጽ ላይ ባለፈው ሳምንት ሐሳባቸውን የሰጡ የሀገራችን የፊልም ተመልካቾች ፊልሞቹ ተመሳሳይ ከመሆናቸው በተጨማሪ ‹‹ፊልሞቹን ቀድመን የምንተነብያቸው ናቸው››ብለዋል፡፡ ‹ቀጥሎ እንዲህ ይሆናል› የምንላቸው፣ ቀድመን ያየናቸው የሚመስሉ፣ ተመልካቾችን ያልቀደሙ የአሰልች ትዕይንቶች ስብስብ ናቸው›› ብለዋል፡፡

ለአብመድ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመልካቾች አብዛኞቹ ፊልሞች የወንጀል ድርጊትን የሚያስተምሩ፣ ከሴት እና ወንድ ፍቅር መሥራት ውጭ የተለየ ይዘት ያለው ፊልም መሥራትን የረሱ ናቸው እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡ 80 በመቶ ገበሬውን እና የሀገሬውን እሴት፣ ታሪክ እና አፈ ታሪክ ረስተው በምዕራባውያን ሕንጻዎች ሰማይ የተንጣለሉ ኑሮዎችን ያሳያሉ፡፡ ‹‹ይህ የእኛ ሕይወት አይደለም፤ በፊልሞቻችን በኩል ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ታሪክ የለንም›› የሚሉት ተመልካቾቹ የኢትዮጵያ ፊልሞችን ከሀገሪቱ የዕድገት ደረጃ በማነጻጸር ይከራከራሉ፡፡

አስተያዬት የሰጡ የፊልም ተመልካቾች ‹‹ምን ፊልም ብቻ፤ ማን ኢትዮጵያዊ መምህር አለ? በእንግሊዝኛ ተምሮ በአማርኛ ሲሠራ የሚደበላለቅበት ሰው፤ ማን ነው ኢትዮጵያዊ? የትኛው ዶክተር ነው የውጭ ሕክምናን ያስቀረው? የትኛው እግር ኳስ ቡድን ነው ስማችንን ያስጠራው? የትኛው የውኃ መሐንዲስ ነው እናቶቻችንን እንሥራ ከመሸከም የታደገው? የትኛው የፈጠራ ባለሙያ ነው አገራችንን ከሁለት ሚሊዮን ዓመታት በላይ ስትጠቀምበት ከኖረችበት እርሻን በበሬ ማረስ ያስቀረ? የትኛው አምራች ነው አገራችንን ከውጭ ጥሬ ዕቃ እንዳታስገባ ያደረገው? የትኛው የመንግሥት መዋቅር ነው ሠላም አስፍኖ የቱሪስት መዳረሻ ያደረገ?›› ሲሉ ሀገራዊ ችግራችን ከፊልሞች ላይ ብቻ አለመንጠልጠሉን አንስተዋል፡፡ ይህን አስተያየት አብዛኛው ተዋናዮች ወይም ደራሲዎች ተቀብለው ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያዊ መልክና ቃና እንዲኖራቸው ከመሥራት ይልቅ ሐሳብ ሰጭዎችን ለመሞገት ሲጥሩ እንደሚታዩም አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ የፊልም ሠሪዎች ብቻ ችግር አይመስለንም›› የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ ጉዳዩን ሲያስረዱ ‹‹ለአብነት ጤዛ ፊልም ለዕይታ ሲበቃ እየተሳለቁ ሳይጨርሱት የወጡ ብዙ ቧልት የናፈቃቸው ሰዎች ነበሩ›› ብለዋል፡፡ ጤዛ ፍጹም ኢትዮጵያዊ እሴት ያለው ፊልም መሆኑን እንደሚያምኑ የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ ‹‹ደራሲዎች የሚያቀርቧቸው ተመልካቾች  የሚቀበሉትን ነው›› የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቲያትር እና ፊልም ጥበባት መምህር አስናቀው ዓለሙም የኢትዮጵያ ፊልሞች ገና ሲጀምሩ ዓይቶ መጨረሻቸውን ማወቅ የሚያስችሉ ተመልካቾችን ያልቀደሙ ትዕይንቶች እንደሚበዙባቸው ተናግረዋል፡፡ መምህሩ ‹‹የእኛ ፊልሞች ኅብረተሰቡን ሳይሆን ሠሪዎችን ብቻ ነው የሚመስሉት›› ብለዋል፡፡  አብዛኞቹ ፊልሞች የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን እሴት እና ባህል መግለጥ አለመቻላቸውን የተናገሩት መምህሩ ‹‹ፍቅርን ማጠንጠኛ አድርገው የሚሠሩ ፊልሞቻችን ቧልታቸው (ሳቅን የሚፈጥሩበት) መንገድ አብዛኛዎቹ ኢ-ሞራላዊ ናቸው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ፊልሞች የሰዎችን ባሕሪ የሚቀርጹ፣ በመልካም ጎናቸው የሚስሉ፣ የኪነ ጥበብን ማኅበራዊ መሞረጃነት የሚጎሉ ናቸው›› ብለዋል፡፡

ዘርፉ በኢትዮጵያ ያልተነካ እምቅ አቅም መሆኑን ያመለከቱት መምህሩ ትውፊታዊ ፊልሞችን ለመሥራት ስንፍና ስለሚጠናወታውና ፍቅረ ነዋይ በዝቶባቸው ቀላል መቼትን የሚፈልጉ ፊልም ሠሪዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ፊልሞቻችን ታሪክን መከተብ የማይችሉ ስለሆኑ መንግሥት ሊያግዛቸው ይገባል፡፡ ‹‹መንግሥት ሕዝቦቹን ብቻ ሳይሆን የሕዝቦቹን እምቅ ሀብት፣ ጸጋ፣ ዕውቀት እና ልማድ፣ የመልካም ዜጋ መቅረጫ፤ የኢኮኖሚ አማራጭ ለማድረግ ከአደረጃጀት እስከ ሀገርን ማስተዋወቅ ሊጠቀምበት ይገባል›› ብለዋል፡፡

የሀገሪቱ ባለሀብቶች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ለዘርፉ ድጋፍ በማድረግ ለፊልም ኢንዱስትሪው ማደግ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ኢንዱስትሪ ባለሙያና የአማራ ክልል የቴያትር እና ፊልም ማኅበራት ፕሬዝዳንት አብቹ ኃይለማርያም ‹‹እሴቶችን ያደበዘዙ፤ ለንዋይ የቋመጡ፣ ዘመን የማይሻገሩ ፊልሞች እንዲበራከቱ የመንግሥት ቸልተኝነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለፊልም ኢንዱስትሪው ትኩረት አለመስጠቱን የተናገሩት አቶ አብቹ ‹‹የፊልም ኢንዱስትሪ የግለሰቦች ጥረት ብቻ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ እሴት፣ ባህል፣ ልማድ ታሪክ እና አፈ-ታሪኮች ዘመን ተሻጋሪ ሁነው መቅረብ አልቻሉም›› ይላሉ፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ እንደደርግ ዘመን ኢትዮጵያዊ እሴቶች እና ታሪኮችን ወደፊልም እንዲቀየሩ ያደረገ መንግሥታዊ መዋቅር የለም›› ያሉት አቶ አብቹ በደርግ ዘመን የአባተ መኩሪያ እና የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ‹ዓድዋ› ታሪካዊ ፊልሞች እስከዛሬ የሚጠቀሱ ትልልቅ ሥራዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ማንነቶች ላይ ተሠርተው ሶሻሊስት ሀገራት ላይ የመታየት ጅምሮችም እንደነበሩ አስታውሰዋል፤ በደርግ ዘመን የፊልሞች ዕድገት እና ይዘት እንዲጠበቅ ‹የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን› የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚያ ዘመን በአማራ ክልል እንኳ በደብረ ማርቆስ፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ሲኒማ ቤቶች ተቋቁመው ነበር›› ያሉት አቶ አብቹ የኢሕአዴግን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የፊልም ኮርፖሬሽኑ እና በየከተሞች የተቋቋሙ ማሳያ (ሲኒማ) ቤቶች እንደተዘጉ አመልክተዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ተቋማት እና ለፊልም አዲስ ምዕራፍ የሚያስቡ ባለሙያዎችን መንግሥት እንዲደግፍም አሳስበዋል፡፡ ፊልሞች በባሕል ፌስቲቫሎች እንዲካተቱ፣ ቀለማቸው የታወቁ የታሪክ፣ የእሴትና ልማድ ማንፀባረቂያ እንዲሆኑ እንደሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ፀጋዎች በተዘዋዋሪ ብድር ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት አሠራር እንዲፈጠር መንግሥት መሥራት እንደሚኖርበትም አቶ አብቹ ተናግረዋል፡፡

ዓውደ ጥናቶችን በማካሄድ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጡ ለባለሙያዎች አጫጭር የሀገር ውስጥና የውጭ ስልጠናዎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት ከመንግሥት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያዊ እሴት ወደ ምዕራባውያን ያማተረውን የፊልም ኢንዱስትሪ የቁልቁለት ጉዞ ለመግታት በየመካከሉ ከሚሠሩ ድንቅ ፊልሞች ውጭ ንዋይን ማዕከል ላደረጉት አሠራሮች መለወጥ የሚበጅ ወጥ የሆነ ፖሊሲ አልተፈጠረም፡፡ በኢትዮጵያ በ1994 ዓ.ም የባህል ፖሊሲ በ2010 ዓ.ም ደግሞ የፊልም ፖሊሲ ቢወጣም ዛሬም በመንግሥት ጓዳ ውስጥ ብቻ ያለና ወደ መሬት ያልወረደ ነው፡፡ ሁለቱን ዘውጎች ያጣመረና በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት እና በአንድ ፊልም ከሁለት በላይ ሙያዎችን ይዘው የሚሠሩ ግለሰቦችን ቁጥር መቀነስ አንዱ የመፍትሔ ሐሳብ ነው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ በጀት መመደብ እና እንደ አንድ ተቋም መክፈት የቀጣይ የቤት ሥራዎች ከሆኑ ዘርፉ የትውልድ መቅረጫ ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡

በእናንተ ዕይታ በምን መንገድ ቢሠሩ የኢትዮጵያ ፊልሞች ትንሳኤ ሊመጣ ይችላል?  ሐሳብ ስጡበት፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here