“የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በጥንቃቄ እየተከላከልን ልጆቻችንን ትምህርት ቤት እያስመዘገብን ነው፡፡” ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አብመድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች

0
9

ባሕር ዳር፡ መስከረም 06/2013ዓ.ም (አብመድ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ከተወሰዱ የቅድመ መከላከል እርምጃዎች መካከል ትምህርት ቤቶችን መዝጋት እና ተማሪዎች ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የትምህርት ዘርፍ ለማስጀመር በአማራ ክልል ከመስከረም 4/2013 ጀምሮ ትምህርት ቤቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ በማድረግ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ አቅጣጫ ተቀምጦ ምዝገባ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አብመድ ያነጋገራቸው የተማሪ ወላጆችም ጥንቃቄ በማድረግ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመውሰድ እያስመዘገቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ ከዳንግላ ዙሪያ ወረዳ ጊሳ ቀበሌ አብመድ ያነጋገራቸው አቶ ገነት ወልዴ እና ቄስ ፀጋ ደስታ “የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በጥንቃቄ እየተከላከልን ልጆቻችንን ትምህርት ቤት እያስመዘገብን ነው” ብለዋል፡፡ መንግሥት ደግሞ ልጆቻቸው ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተጨማሪ ክፍሎችን ማመቻቸት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የዳንግላ ወረዳ የጫራ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእስ መምህር ገዙ የሺዋስ ለወረርሽኙ ተጋላጭነትን በመቀነስ ምዝገባ እያካሄዱ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ርእሰ መምህሩ ተማሪዎች ለመመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ርቀታቸውን እንዲጠብቁና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲጠቀሙ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱም ከወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን የቅድመ መከላከል ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መቼና በምን ሁኔታ? ትምህርት እንደሚያስጀምሩ ገና አለመወሰኑን ርእሰ መምህሩ ተናግረዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዓለሙ ክህነት ደግሞ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በቅድመ መደበኛ 50 ሺህ 515፣ ከአንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል 291 ሺህ 230፣ ከ9 እስከ 12 ክፍል 74 ሺህ 728 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ እንደኃላፊው መረጃ ከመስከረም 4 እስከ 8/2013 ዓ.ም ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ክፍል ተማሪዎች እየተመዘገቡ ነው፤ ከመስከረም 11 እስከ መስከረም 15/2013 ዓ.ም ደግሞ ነባር ተማሪዎች ካርድ በመውሰድ እንደሚመዘገቡ አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩት ኃላፊው ከወላጆች ተለይተው ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ትምህርት ቤቶች የጥንቃቄ ዝግጅት እያደረጉ መሆንኑን ገልጸዋል፡፡ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችንም ሀገራዊ አቅጫ ሲሰጥ ማካካሻ ትምህርት ተሰጥቶ ፈተና ስለሚወስዱ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here