የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

0
26

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከዓለም ሕዝብ 15 በመቶ ያህሉ በተለያዩ የአካል ጉዳተኝነት ሁኔታ እንደሚኖሩ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በቀዳሚነት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ የሚመለከታቸው አካላት እያሳሰቡ ነው፡፡ አንዳንዶች ቫይረሱን ለመቆጣጠር መሠረታዊ የንጽሕና ርምጃዎችን የመተግበር ችግሮች ሊኖሩባቸው ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እንክብካቤ ወይም ሌላ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው ማኅበራዊ ርቀትን መለማመድ ላይችሉ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም መረጃው የሌላቸው በርካቶች ሊሆኑም ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ በቫይረሱ የሚያዙ አካል ጉዳተኞች በሽታውን የመቋቋም አቅም ወይም ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተዛመደ ችግራቸው ጋር ተዳምሮ ነገሮች የከፉ ሉሆኑባቸው ይችላሉ፡፡ የአካል ጉዳተኞች ቀደም ብሎ በተጠቀሱት ምክንያቶች አካዊ መራራቅን መተግበር ባለመቻላቸው በኮሮና ቫይረስ የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡

በጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ አካል ጉዳተኞች የሙያ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ በዚህ ዙርም ለአራት ወራት የተግባር ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ አካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ ወጣት ዋሴ መኩሪያው በክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከሉ የልብስ ስፌት ሰልጣኝ ነው፡፡ በማዕከሉ ስለኮሮና ቫይረስ መተላለፊያና ቅድመ መከላከያ ዘዴዎች ባገኘው ግንዛቤ መሠረት ጤናውን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ለአብመድ በስልክ ተናግሯል፡፡ ማዕከሉ ለሰልጣኞች ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ እንደውኃ፣ ሳሙናና አልኮል ያሉ የንፅህና መጠበቂያዎችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡ ሌሎች የማዕከሉ ሰልጣኞችም “ታሞ ከመማቀቅ …” በሚል ቅድመ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ትዝብቱን አካፍሎናል፡፡

ልክ በማበልፀጊያ ማዕከሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች እየተፈጠረላቸው እንዳለው ግንዛቤ ሁሉ ለሌሎች አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችም ሊሠራ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ለጉዳት ከመዳረግ በፊት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አቶ ዋሴ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ትኩረት ለሚሹ ወገኖች ከዚህ በፊት ሲያደርጉት የነበረውን አለኝታነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ጠይቋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ዘር፣ ቀለም ሳይለይ ሁሉንም የሰው ልጆች ለኅልፈት እየዳረገ ያለ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች፣ የጎዳና አዳሪዎች፣ አረጋውያን እና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለኮሮና ቫይረስ የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ የተናገሩት የአማራ ክልል ሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ልማት ደኅንነት ማስፋፊያ ዳይሬክተር በላይነው ፀጋ ናቸው፡፡ እንደአቶ በላይነው ገለፃ መሥሪያ ቤታቸው ለአካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና አዳሪዎችና ለሴተኛ አዳሪዎች ስለቫይረሱ መተላለፊያና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች የሰጠው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለየ በበሽታው የመጠቃት ዕድል ስላላቸው ትኩረት ተሰጥቶ የመሥራት ጅምር ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ ተቋማዊ መዋቅሩን ጠብቀውም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የሚመለከታቸው አጋር አካላት እና ኅብረተሰቡ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ስለሚሆኑ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶክተር) በተቋማቸው ማኅበራዊ ገጽ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የአካል ድጋፍ የሚጠቀሙና የእንቅስቃሴ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ መሣሪያዎቻቸውን በደንብ ማጽዳት እንደሚኖርባቸውም ሚንስትሯ አሳስበዋል፡፡

ስለኮሮና ቫይረስ ያለው መረጃ በተገቢው መንገድ እንዲደርሳቸው የብዙኃን መገናኛ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here