“የወረታ ወደብ ዋና ዓላማ የሱዳን ወደብን (ፖርት ሱዳን) ለመጠቀም ነው፡፡”    ርእሰ መስተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ

0
29

የፌዴራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ከሱዳን ገዳሬፍ ግዛት ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የወረታ ደረቅ ወደብ የተገነባበት ዋና ዓላማ የሱዳን ወደብን (ፖርት ሱዳንን) ለመጠቀም መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ናቸው፡፡ በወደቡ አካባቢ የተሰጠ መሬት እንዳለና እንደሚለማም አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከርና ሠላምን ማስጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡ ይህም ወደ ውጭ ለሚላኩ ምርቶችና ከውጭ ወደ ውስጥ ለሚገቡ የግብርና ምርቶች ፋይዳው የጎላ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

የታጠቁ ኃይሎችን፣ ሽፍቶችና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትን ለመከላከል ሁለቱም ክልሎች የጋራ የፀጥታ ኃይል ለማሰማራትና ለመሥራት መግባባት ላይ እንደደረሱም አቶ ተመሥገን አሳውቀዋል፡፡ በተመሳሳይ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን ለመግታት ጠንካራ ፍተሻና መከላከሉ ላይ ለመሥራትም ተስማምተዋል፡፡ የመረጃ ልውውጥ በማካሄድ ጭምር እንደሚሠራ አቶ ተመሥገን አንስተዋል፡፡

የገዳሬፍ ግዛት ርእሰ መስተዳድር ሜጀር ጀነራል ነስረዲን አብዶልቀዩም በድንበር አካባቢ የስርቆት፣ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ (ኮንትሮባንድ) እና ሌሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ ዝግጁነቱ የታየበትና መስማማት ላይ የተደረሰበት ውይይት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በንግዱ ዘርፍ ኢትዮጵያ የሱዳን ወደብ (ፖርት ሱዳን) እንድትጠቀምና አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጅት እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር በማኅበራዊና ባህላዊ መስኮች ተሳስሮ ለመቀጠል ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን የገዳሬፍ ግዛት ርእሰ መስተዳድር ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት ሀገሮችና የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ይበልጣል አዕምሮ የምክክሩ ዓላማ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጤናማ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን የበለጠ ማጎልበትና በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ዛሬ ሁለቱ ክልሎች እንሠራባቸዋለን ካሏቸው ጉዳዮች መካከል ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር አንዱ ነው፡፡ ጉዳዮ በኢትዮጵያ አስጊና አሳሳቢ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ በፊት የጦር መሣሪያዎቹ ከሚገቡባቸው መስመሮች ጅግጅጋ፣ ሞያሌ፣ ጋምቤላ እና መተማ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሱዳን በኩል የጦር መሣሪያዎቹ እንደገቡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በዚህ ጊዜም የፍተሻ ቴክኖሎጂ መሳሪያ እጥረትና ፖለቲካዊ ችግሮች ለሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውወሩ መንገድ የከፈቱ ምክንያቶች መሆናቸው ቢነሳም ተግዳሮቱን ለመፍታት መስማማት ላይ ተደርሷል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ግንኙነቱን ለመምራት ከተፈረሙ ስምምነቶች አንዱ የሁለቱ ሀገራት የጋራ የድንበር ልማት ኮሚሽን ነው፡፡ በኮሚሽኑ ስር ተጎራባች ክልሎች በየሦስት ወሩ እየተገናኙ በልማት፣ ፀጥታና ሠላም ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ያሳያል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here