የዓምደ ጽዮን አሻራ፤ የ700 ዓመታት ሙሽራ፡፡

0
59

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 21/2012ዓ.ም (አብመድ) ጣናን በአጠገቧ እየተመለከተች፣ በማዕበሉ ዝማሜና በአዕዋፋት ዝማሬ ታጅባ ሰባት ክፍለ ዘመናትን ያለፈ ታሪክ ያቀፈች ታላቅና ታካዊት ስፍራ ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነቷና ባሕላዊነቷን አልለወጠችም፤ ጥንት ባለችበት በሳር ክዳን ዛሬም ድረስ አለች፡፡ የሠሪዋን አሻራ ያልለወጠች የ700 ዓመታት የሳር ጎጆዋ ደብረ ሲና ማርያም ገዳም፡፡

በዘመኑ ዓፄ ዓምደ ጽዮን ነግሠው ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ ነበር፡፡ ንጉሡ መልካምና ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ልቦና ያላቸው እንደነበር ገድላቸው ያስረዳል፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በርካታ ድንቅ ድንቅ ሥራዎችን ለትውልድ ጥለው አልፈዋል፡፡ በ1312ዓ.ም በማሩ ቀመስ ደንቢያ ወለል ባለው መስክ ወርደው በጎርጎራ መዳረሻ ከጣና ሰገነት ላይ አንዲት ደብር ደብረዋል፤ ስያሜዋም ደብረ ሲና ማርያም ትባላለች፡፡

ወደ ገዳሟ ሲገቡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሙሽራዋን ለዓመታት ሲያጅቡ የኖሩት እድሜ ጠገብ ዕፅዋት ቀልብን ይስባሉ፡፡ ከዛፎቹ ግርጌ አልፎ ወደውስጥ ሲቀርቡ ደግሞ በዚያ ዘመን የነበረውን መልኳንና አሠራሯን ያልቀየረች አስደናቂ የሳር ክዳን ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች፡፡ ምናልባት የሳር ጎጆዋን ሲመለከቱ ‹‹ይህቺስ በቅርብ የተሠራች ደብር ናት፡፡ በዚህ ዘመን በሳር የተለበሰች ደብር እንዴት ተገኘች?›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው 700 ዓመታትን በሳር ክዳን አሳልፋለች፤ አያሌ ታሪኮችንም ተሻግራለች፡፡

በደብረ ሲና ገዳም ውስጥ ዘመናትን ያለ እድሳት የተሻገሩ ታሪካዊና መንፈሳዊ ስዕለ አድኅኖዎች ይገኛሉ፡፡ ገዳሟ በዓፄ ዓምደጽዮን አማካኝነት በጻዲቁ አባ ቶማስ እንደተሠራች ይነገራል፡፡ በጭቃና በድንጋይ በጥበብ የተሠራችው ደብረ ሲና ማርያም የሳር ክደኗ በሌላ ሳር ከመቀየሩ በቀር ሌለው በዘመኑ እንዳለ አሁን ይገኛል፡፡

ከቤተ ክርስቲያኗ አናት ላይ በሰጎን እንቁላል የተንቆጠቆጠው ጉልላት የደብሯ የተለዬ ውበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ስትሠራ ‹‹ጣናም አግዟል›› ይባላል፡፡ ‹‹አሁን ድረስ ምሰሶ ሆኖ የቆመ እንጨት በማዕበል አምጥቶ ደብሯ ከተሠራችበት ስፍራ ላይ ጥሏል›› ይባላልና፡፡

እነሆ ይህች ታሪካዊት ደብር ትናንት የተደበረችበትን 700ኛ ዓመት አክብራለች፡፡ ዓመታዊ በዓሏን ከማክበርና 700ኛ ዓመቷን ከመዘከር ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ሰሞኑን ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡ በቀጣይም ጎርጎራና አካባቢዋን የቱሪስት ፍሰቱ የበለጠ እንዲጨምር ለማድረግ እንደሚሠራም ታውቋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here