የደብረ ታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎችን የሙቀት ልዬታ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

0
24

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሠራ መሆኑን የደብረ ታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል አስታወቀ።

የደብረ ታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።

ሆስፒታሉ ከትናንት ጀምሮ ደግሞ የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችን በማስገባት ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ተገልጋዮችን የሙቀት ልኬታ እያደረገ መሆኑን ሚዲካል ዳይሬክተሩ ገብሬ ድንቃየሁ (ዶክተር) ለአብመድ ተናግረዋል።

‘‘ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች እንደምንረዳው የስርጭት መጠኑ ከሚስፋፋባቸው መካከል የሕክምና ተቋማት ናቸው’’ ብለዋል ዶክተር ገብሬ፡፡ ሆስፒታል ሰዎች ለሕክምና በብዛት የሚሰበሰቡበት በመሆኑ ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማን አንድ አስታማሚ ብቻ እንዲኖር፣ ሕሙማንን ሊጠይቁ የሚመጡ ሰዎች እንዳይገቡ በመከልከል እና ለሕክምና የሚገቡ ሰዎችንም የልየታ ቦታ በማዘጋጀት የሙቀት ልኬታ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየተሠራ እንደሆነም ገልፀዋል። እስካሁን የሙቀት ልኬታ ከተደረገላቸው ከ200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠረጠረ ሰው አለመኖሩንም ዶክተር ገብሬ ተናግረዋል።

አካላዊ ጥግግትን ለማስወገድ ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ሰዎች ከውጭ በ2 ሜትር ርቀት ላይ የመሰለፊያ ቦታ ተዘጋጅቶ እጃቸውን እየታጠቡ እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ሰዎች ከነበራው ማኅበራዊ እሴት የተነሳ ርቀቱን እየጠበቁ ባለመሆኑ የኮሮና ቫይረስ የመተላለፊያ መንገዶቹን ተገንዝበው ራሳቸውን እና ማኅበረሰቡን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ እንደሚገባ ሚዲካል ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት፣ በሕክምና ባለሙያዎች እና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ ትክክለኛ መረጃዎችን ወስዶ መከላከያ መንገዶቹን ተግባራዊ በማድረግ እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ዶክተር ገብሬ አስታውቀል።

‘‘ማኅበረሰቡ መፍራት ሳይሆን መጠንቀቅ አለበት፤ ፈጣሪ ይጠብቀኛል ብሎ መዘናጋት በየትኛውም ሃይማኖት የሚደገፍ ባለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል’’ ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ይህ ግን እምነት አያድንም ማለት እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

በሆስፒታሉ ለሕክምና አግልግሎት ያገኘናቸው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ አቶ ንጉሤ ዓለማየሁ እና ወይዘሮ ፈንታነሽ ዓለሙ በሃይማኖት ተቋማት እና በመገናኛ ብዙኃን ስለቫይረሱ መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶች ግንዛቤ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባገኙት የግንዛቤ ትምህርት መሠረትም ቤተሰቦቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው በቫይረሱ እንዳይያዙ የመከላከያ መንገዶችን እየተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ እንደየእምነቱ ፈጣሪውን በማመሥገን ቫይረሱ እንዲጠፋ መጸለይ እንደሚገባው እና የመተላለፊያ መንግዶቹን አውቆ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ -ከደብረ ታቦር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here