‹የጉራጌ መስቀሎች›

0
152

 

አቅጣጫችንን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አድርገናል፤ የጉዟችን ዓላማ ደግሞ የመስቀል በዓልን ለማክበር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በጉራጌ ብሔረሰብ የመስቀል በዓል አንድ አይደለም፡፡ በርከት ያሉ የመስቀል በዓልን በቀያቸው ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለማክበር የሚጓዙ ሰዎችን በማግኘቴ ከበዓል ጋር የተያያዙ ወሬዎችን እየተጨዋወትን በምናብ ወደ ጉራጌ ዞን እንጓዝ፡፡

አብረውኝ የሚጓዙት አብዛኞቹ ከጉራጌ አካባቢ የመጡ ሰዎች በመሆናቸው የአካባቢውን የመስቀል በዓል ትውፊት ለመገንዘብ ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ በጉዟችን መሀል ጥያቄዎች እያነሳሁ መጨዋወታችንን ቀጥለናል፡፡ መስቀል በጉራጌ ትልቅ ስፍራ እንደሚሰጠው ሁሉም እየተቀባበሉ በተለያዩ አገላለጾች አወጉኝ፤ መስቀል ለጉራጌ ማኅበረሰብ እጅግ ተናፋቂ በዓል ነው፡፡

ዓመቱ አልቆ የመስቀል በዓል እስኪደርስ ድረስ ጊዜው ይርቃል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ሲናፍቁ ይከርማሉና፡፡ ዓመቱ ሲደርስ ታዲያ በጤና ያለ ሁሉ ወደ ተወለደበት ስፍራ ይጎርፋል፤ በተወለደበት ቀዬም ይሰባሰባል፡፡ በመስቀል የቀረ እራሱም ያዝናል፤ ወዳጅ ዘመዱንም ያሳዝናል፡፡ በባሕሉ መሠረት የመስቀል መቅረት መልካም አይደለም፤ እያሉ እያጫወቱኝ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡

መስቀል በኢትዮጵያውያን እጅግ ደማቅ በዓል ቢሆንም በጉራጌ ብሔረሰብ ግን የተለዬ ድምቀት እና ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ መስቀል በጉራጌ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባሕላዊ አንድምታም ያለው በዓል ነው፡፡ የመስቀል ዕለት ያለው የአመጋገብ ሥርዓት፣ የዘመድ ጥየቃው እና ሌሎች ክዋኔዎች የተለዩ ናቸው፡፡ አሁን ጉዞየን አጠናቅቄ ከጉራጌዎች ቀየ ደርሻለው፤ ስለመስቀል እና ተያያዥ ወጎች ግን በአካባቢው ሰዎች የሚደረግልኝ ገለጻ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

መስቀል በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ መከበር የሚጀምረው ከመስከረም 12 አንስቶ ነው፡፡ በመስከረም 12 እና 13 ማጽዳት፣ ራስን ማስዋብና ሌሎችም ተግባራት ይከወናሉ፡፡ ዛሬ መስከረም 14/2012 ዓ.ም ደግሞ በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ ‹‹የሴቶች ቀን›› ወይም ‹‹የሴቶች መስቀል›› በሴቶች ዘንድ እንደሚከበር ተነግሮኛል፡፡ በዚህ ቀን በሴቶች ላይ ማንም ጣልቃ አይገባባቸውም፡፡ ቀኑ የእነሱ ነው እና ልዩ አድርገው ያከብሩታል፡፡ በዚህ ቀን ወደ ቀየዋ ጎራ ብላ ወዳጅ ዘመዱን ያላከበረች ሴት አንዳች ችግር ቢገጥማት ነው ተብሎ ከልብ ይታዘናል፡፡

በዚህ  የሴቶች ቀን የጎመን ክትፎ የሚዘጋጅበት ዕለት ነው፡፡ የጎመን ክትፎው በቅቤና በተለያዩ ቅመማቅመሞች የሚዘጋጅ አስደናቂ ባሕላዊ ምግብ ነው፡፡ ምግቡ የፍስክ በመሆኑ መስከረም 14 ረቡዕ ወይም ዓርብ የሚውል ከሆነ የጎመን ክትፎው አንድ ቀን ቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ የዘንድሮው መስከረም 14 ረቡዕ ቀን የዋለ በመሆኑ የጎመን ክትፎው የተዘጋጃው ማክሰኞ ማታ ነው፡፡ ቀኑ ግን ያው የሴቶች ቀን ነው፡፡ በሴቶች ቀን የሚዘጋጀው ክትፎ መስከረም 15 ለሚደረገው የእርድ ዝግጅት መቀበያ ይውላል፡፡ የጎመን ክትፎው  በመስቀል ዕለት የሚጣለውን ፍሪዳ ተከትሎ ልጆች እንዳይታመሙ የቅድመ ሆድ መጥረጊያ እና ከህመም መከላከያም  ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ቀን የጉራጌ ባሕላዊ ምግብ ቆጮም ይዘጋጃል፡፡

የጎመን ክትፎውና ቆጮው ከተዘጋጄ በኋላ ከትልልቅ ከብቶች ቀንድ በሚዘጋጅ ‹‹አንቀፋ›› በሚባል ባሕላዊ የመመገቢያና ምግብ የማደያ ዕቃ ይቀርብና ለቤተሰቡ ይታደላል፤ በጉራጌኛ ‹‹ጊፍት›› ይሉታል፡፡  በዚህ ምግብ ሆዱን የጠረገ ሁሉ በ15 የሚታረደው የከብት ስጋ እንደማያመው ይታመናል፡፡ መስከረም 14 ወንዶች ድርሻቸው መመገብ ብቻ ነው፡፡ መስከረም 15ን ደግሞ ‹‹የወንዶች በዓል (የወንዶች መስቀል)›› ይሉታል፡፡

በዕለቱ የሚደረገውን የእርድ ሥነ-ስርዓት እስከ አብስሎ መመገብ የሚያደርሱት ወንዶች ናቸው፡፡ በቀን 15 በሚደረገው የእርድ ዝግጅት ሴቶች ቆጮ ከመጋገር የዘለለ በስጋው ዝግጅት አይሳተፉም፡፡ መስከረም 16 በደመራው ቀን የቀየውን ሕዝብ በሚያገናኘው የደመራ ሥነ-ስርዓት ተገናኝተው ባሕላዊ መጠጦች እና ባሕላዊ ምግቦችን በመመገብ ሴት ወንዱ፣ ታላቅ ታናሹ በጋራ ያከብራሉ፡፡ በዚሁ ቀን በጤና ካደረሳቸው ‹ለቀየው ሕዝብ አስረክባለው› ያሉትን ስለት ‹እንካችሁ› ይላሉ፡፡

የጉራጌ ሕዝብ መስከረም 17 በሚደረገው የሻኛ በዓልም የቀየው ሰው በዕድሜ ከፍ ካሉ እማ ወራና አባውራ ቤት ተገናኝተው ከአባቶች ምርቃት ከተቀበሉ በኋላ በጋራ እየተመገቡ በድምቀት ያሳልፉታል፡፡ መስቀል በጉራጌ በቀናት ልዩነት የሚያልቅ በዓል አይደለም፡፡ እስከ አንድ ወር ገደማ ይዘልቃል፡፡ ከተለያዩ ሀገራትና አካባቢ የመጡ የቀየው ተወላጆች ለሥራ በመጡ በሁለት ሳምንት አጠረ ቢባል እንኳን በአንድ ሳምንት ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ኑሯቸውን በዚያው ያደረጉ ወላጆችና ልጆች ግን ለመስቀል ስጦታ የመጣላቸውን አዳዲስ ልብስ እየለበሱ፣ በመስቀል የታረደውን የከብት ቋንጣ እየሠሩ፣ ቡና እያፈሉ ከዘመድ ጎረቤት ጋር እየተጠራሩ ለአንድ ወር ያክል በዓሉን ያከብሩታል፡፡ መስቀል በጉራጌ የተጫጩ ፍቅረኛሞች የሚጋቡበት በዓልም ነው፡፡

በዓለፈው መስቀል የተጫጩ ፍቅረኛሞች ዓመቱን ጠብቀው በዓሉ ሲደርስ ይጋባሉ፡፡ በመስቀል በዓል ሠርግ አይታጣም፡፡ ልጃገረዶችም በሙሽሮች ቤት እየተዘዋወሩ የባሕሉን ጭፈራ እየጨፈሩ በዓሉን ያደምቁታል፡፡ እኛም በቀሪ የጉራጌ የመስቀል በዓል ቀናቶች የሚከወኑትን ክዋኔዎች ለመመልከት እየጠበቅን እስከ በዓሉ መጨረሻ አብረን እንዘልቃለን፡፡ ኢትዮጵያ ድንቅ ናት፤ ድንቅም አላት፤ ድንቅም ታደርጋለች፡፡ ከሕዝቦቿ የሚጠበቀው በሠላምና በአንድነት ኢትዮጵያን ማነጽ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን መንገዱ ሁሉ ስሉ ይሆናል፤ ሰላም፡፡ መልካም በዓል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here