የጋዜጠኛው ትዝብት በዋግ ኽምራ፡፡

0
84

የጋዜጠኛው ትዝብት በዋግ ኽምራ፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2012 ዓ.ም (አብመድ) ‹‹አታልቅስ ይለኛል ላልቅስ እንጂ አምርሬ፣
መከራ ባዛለው ዘመን ተፈጥሬ›› እያልኩ ዋግን ከላይ እስከ ታች አየኋትና አዘንኩ፡፡ ይህ ሕዝብ ውለታው ቀርቶ ‹‹የማኅፀን ኪራዩ›› ያልተከፈለለት ሕዝብ ይመስለኛል፡፡

‹‹በክፉ ቀን መጣህ!›› ያሉኝ የቀድሞ ክፍለ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ካድሬ፣ የማረሚያ ቤት ፖሊስ እና የአሁኑ ጡረተኛ ‹ቆስቁስ› አስር አለቃ ክፍሌ ታደሰ ንግግር ይችኑ ልማደኛ ዓይኔን በእንባ ሊያወረዛት አማረው፡፡ ‹‹ወንድ ልጅ አያለቅስም›› የምትለው አባባል ብዙም አትስማማኝ፡፡ ወዳጄ! የማታለቅሰው እኮ የማያስለቅስ ነገር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ‹‹እንኳን መብላት ማብላት ይቀራል›› እንዳለ ደጉ ያገሬ ሰው እንደዚህ እንደ አሁኑ ድርቅን እና እጦትን እንግዳን አብልቶና አጠጥቶ ካለመላክ ጋር አስተሳስሮ የሚያዝን እና ድህነቱን አምርሮ የሚረግም የሰው እርካብ ሲገጥምህ ለምን አታለቅስ? እመነኝ ወንድ ብትሆንም ታለቅሳለህ!

የዋግ ታጋዮች በዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማ ውስጥ የመጀመሪያውን ድርጅታዊ ጉባኤ ባደረጉበት እና ቀድሞ የኢህዴን የጦር መሣሪያ መካዘን በነበረው ፍርጣጣ ዛፍ ዋሻ ዳር ሆነን ከቆስቁስ አስር አለቃ ክፍሌ ደስታ ጋር ብዙ አወራን፡፡ ከርሳቸው ጋር የነበረኝን ቆይታ በሌላ ክፍል አስቃኛችኋለሁ፤ አሁን ወደ ዕይታየ ልውሰዳችሁ፡፡

ዋግን ከስሃላ እስከ ዳህና፤ ከዝቋላ አስከ ጋዝጊብላ፤ ከአበርገሌ እስከ ፃግብጂ አየኋት፤ ድርቅ ደግነታቸውን ብቻ ያልነጠቃቸው ‹ያለምወ!› እያሉ የሚያናግሩ የፍቅር ሰዎች ምድር ናት፡፡ መንደርተኝነት ለሚያምሳት ኢትዮጵያ የቀራት የፍቅር ጓዳ ዋግ ይመስለኛል፤ በዋግ ምድር ሁሉም ‹ያለምወ! የምወድህ!› ይባላል እንጅ ‹ከየት መጣህ? የማን ዘር ነህ?› ተሰምቶ አያውቅም፡፡

በፍቅር እቅፋቸው ውስጥ ሆኜ በምዕናብ ወደ 1960ዎቹ የትግል ዘመናት አዘገምኩ፡፡ ዋግ የተፈጥሮ ሐሩር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አረርም የለበለባት የሀገርን መከራ ተሸክማ ሀገር ያተረፈች ባለውለታ ናት፡፡ የዋግ ሕዝብ የተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ዳፋም ዋጋ ያስከፈለው፤ በከፈለው ልክ ግን ያልበላ ነው፡፡ ለሀገር ነፃነት፣ ለሕዝብ ሠላምና ዴሞክራሲ የአብራክ ክፋይ ልጆቹን ያለስስት ገብሮ በደሙና በአጥንቱ ሀገር ያቆመ ባለውለታ ሕዝብ ነው፤ የዋግ ሕዝብ፡፡ ማሳያየ ከ1960ዎቹ የፖለቲካ ትግል ባያልፍ እመርጣለሁና እሱኑ ላንሳ፤ እንጅ ወደኋላማ ከሄድኩ በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ከፍታና ሠላም፣ እነጄኔራል ኃይሉ ከበደ ለነፃነት የከፈሉትን ተጋድሎ … እያልኩ መቆሚያም የለኝ፡፡

ዛሬ እስከ አያት ድረስ ስሙን የቀየረው የያኔው ኅብረ ብሔራዊት ኢህዴን፣ የመካከለኛው ዘመኑ ብአዴን እና የለውጡ ማግሥት አዴፓ ለአቅመ መንግሥት እስኪደርስ ድረስ ፅንሰቱ፣ ውልደቱ እና ዕድገቱ ዋግ ውስጥ ነበር፡፡ እንደ ቆስቁስ አስር አለቃ ክፍሌ ደስታ ሁሉ ሁሉም የዋግ ሕዝብ ለያኔው ኢህዴን ያለው ዕይታ አሁንም ድረስ ያልጠራ ነው፡፡ አምርረው እንዳይጠሉት ‹‹የወለደ አንጀት›› የሚሉት ነገር ዓይነት፣ እንደ ልጅነቱ በተንሰፈሰፈ ፍቅር እንዳይወድቁለት ያልተከፈለ የወላጅ ብድር ኖሯቸው ከፊል ደመናማ የሆነ ዕይታ ይስተዋልባቸውል፡፡

የዋግ እናት እርጎና ወተቱን እንተወውና መቀነቷን ገመድ አድርጋ ስንት ኪሎ ሜትር አቆራርጣ ውኃ ቀድታ ታጋዮችን ውኃ አጠጥታለች፡፡ የዋግ አባት ልጁን ከመገበር አልፎ ማረሻ ጨብጦ እርፍ አገላብጦ ያመረተውን ምርት ለታጋዮች ምግብ ያለስስት የሰጠ ነው፡፡ ኢህዴን በዋግ ምድር ውስጥ እንደ ቤተ አምልኮ እርስትና ጉልት ያለው ድርጅት ነው፡፡

በወቅቱ የነበረው ሥርዓት ያማረረው መላ የኢትዮጵያ ሕዝብን ቢሆንም ቅሉ 37 ሆነው ለትግል በመረጡት የዋግ ምድር የመጡት ታጋዮች ‹‹ዓላማችን እናንተን እና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ማስከበር ነው›› ሲሏቸው ዋጎች በሙሉ እምነትና ፍቅር አምነውና ፈቅደው እንደ ነፃ አውጪ ድርጅት ኢህዴንን ተቀበሉ፡፡ ኢህዴንኖች ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ መራር የሆነውን የትጥቅ ትግል ሲጋፈጡ መሸሸጊያቸው የዋግ ምድር እና ሕዝብ ነበሩ፤ ‹ባሕር እና ዓሳ› በሚል ጥምረት፡፡ የዋግ ሕዝብ ‹‹ዓሳውን ለማግኘት ባሕሩን ማድረቅ›› ተብሎ የደርግ በትር ክፉኛ አርፎበታል፤ ያንም መከራ ችሎ ድርጅቱን ታድጓል፡፡

ነፃ አውጪዎቹ ያንን መራር የትግል ዘመን አልፈው መሀል ሀገር ድረስ ዘልቀው እስኪገቡ እና ሀገረ መንግሥት እስኪመሠርቱም የዋግ ሕዝብ በፅናት አብሯቸው ዘልቋል፡፡ ለዚህ ምስክር ከራሳቸው ከኢህዴኖች ሌላ መጥራት አያስፈልግ ይሆናል፡፡ ዋጎች በኢህዴን የፀና እምነት ነበራቸው፡፡ መንገድ የመሯቸው ነገ ሕዝባቸው በመንገድ መሠረተ ልማት የዘመናት ችግሩ እንደሚቀረፍ ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ የዋግ እናት በርሃ አቆራርጣ፣ ዳገት ወጥታ እና ቁልቁለት ወርዳ ውኃ ቀድታ ያጠጣችው ነገ ውኃ በቧንቧ ተስቦ ያለድካም ሰውና እንስሶቻቸው ውኃ ሲጠጡ፣ ድርቅ በመስኖ ሲረታ የማየት ሕልም ሰንቀው ነበር፡፡ አርሶ ያገኘውን እንደ ልጆቹ ያካፈለው ነገ ከሚመጣው ልማት እኩል እንደሚካፈል ተስፋ በማድረግ፤ የአካባቢውን ፀጋ ወደ ዕለት ጉርስና የብልጽግና ሀብት የሚለውጥ መንግሥት ለመሥራት ነበር፡፡

የያኔዎቹ ታጋዮች ከድል ማግሥት የመሪነትን ርካብ ሲቆናጠጡ ዋግን በውለታው ልክ ቀርቶ የማኅፀን ኪራዩን እንኳን በአግባቡ የከፈሉት አይመስለኝም፡፡ መሪዎቻችን ጤና ሲርቃቸው እና ፈሪሐ ፈጣሪ ሲያድርባቸው የታሸገ ውኃ፤ ሲናደዱ ለብስጭት ሲደሰቱ ደግሞ ለሐሴት ውስኪ ሲያንቆረቁሩ የዋግ ሕዝብ ግን ዛሬም ከትናንቱ የንፁህ ውኃ ጥማቱ የረካ አይመስልም፡፡ መንገድ መርቶ አገር አቅንቶ መሀል ሀገር ያስገባው ሕዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ በመንገድ እጦት ፀጋውን አልምቶ በአግባቡ የመጠቀም ዕድል የተነፈገው ይመስላል፡፡ የወለደ አንጀት ሆኖባቸው በግልፅ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ትውስታቸው ይህንን ቅሬታቸውን በግልፅ ያሳብቃል፡፡

ከተከዜ እስከ መሽሃ፣ ከመና እስከ አክም ኮርና፣ ከፃር አቦ እስከ ቻና ሚካኤል መሰል ታላላቅ ወንዞችን የታደለው የዋግ ምድር በዓሳ ምርት ምድርህ ‹‹የዳቦ ቅርጫት ነው›› ቢባልም ዳቦው በሰማይ የተንጠለጠለ ተስፋ ብቻ ነው፡፡ በርካታ ወጣቶች በዓሳ ልማት ተሰማርተው በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ለገበያ ትስስር የሚፈለገው መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ‹‹የምን ግዴ›› በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጡ በሂደትም ተስፋ ቆርጠው እንዲተውት በመገደዳቸው ዛሬ የበይ ተመልካች ሆነዋል፡፡ ‹‹ምድርህ በማዕድን የበለፀገ ነው›› ቢባልም ለችግሩ ቀን መድረስ ግን አልቻለም፡፡

በመስኖ የሚለማ መሬት የሚያለማ ወጣት ከማኅፀኗ ያልነጠፈው የዋግ ምድር ከጎኑ የሚያግዝ አጋር የለምና መሬቱም ሰውም ፆም ያድሩ ዘንድ ተፈርዶባቸዋል፤ እነ ተከዜናመሸሃን መሰል ወንዞች ዓመቱን ሙሉ በሸለቆ ውስጥ ይፈስሳሉ፤ ሕዝቡ ከሸለቆው ውኃ የሚያቀብለው አጥቶ በድርቅ ይቆላል፡፡

ከዘመኑ ጋር በማይመጥን የዳስ መማሪያ ክፍል እና ያለግብዓት የሚማረው ተማሪ በአካል ብቻ ሳይሆን በአዕምሮም እንዲቀነጭር የተፈረደበት ይመስላል፡፡ በእርግጠኝነት የምናገረው በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነው ግን አሁንም ዋጎች ብርቱነታቸው አለ፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ እየታተሩ ያሉ ናቸው፡፡

‹‹ዕርዳታ›› ሲባል ዋግ ቀድሞ ትዝ የሚላቸው በርካቶች ቢሆኑም እሱ ግን ከነባራዊ ሁኔታው ፍፁም የራቀ ነው፡፡ የዋግን ሕዝብ ችግር ለመፍታት ዕርዳታ ሳይሆን የዋግን ፀጋዎች ከልብ ማልማት ዘላቂ መፍትሔ የሚያደርግ ጠፋ እንጅ፡፡ እንደገባኝ ‹‹ተረጂ›› መባል ለዋግ ሕዝብ ሕመሙ ነው፤ በመሠረተ ልማት አደራጅቶ በፀጋዎቹ ተጠቃሚ የሚያደርገው መንግሥት ይፈልጋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here