የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

0
18

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 30/2012ዓ.ም (አብመድ) የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት በሐይቅ ላይ ትራንስፖርት አገልግሎት 3 ሚሊዮን 813 ሺህ 382 ብር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡

ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ጎብኝዎች፣ ከዕቃ ማጓጓዝ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም ከወደብ ኪራይ የተገኘ መሆኑን ከጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ የተጠቀሰውን ገንዘብ የተገኘው እስከ ሕዳር መጨረሻ ነው፡፡

ከተገኘው ገቢ መካከል 1 ሚሊዮን 49 ሺህ ገደማ ብሩ በጣና ሐይቅ ደሴቶች የሚገኙ ገዳማትን ከጎበኙ የሀገር ውስጥ ጉብኝዎች የተገኘ ነው፤ ከውጭ ሀገራት ጎብኝዎች 872 ሺህ 743 ብር እንደተገኘም ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጅ ድርጅቱ የትራንስፖርት አሰጣጡንም ሆነ የወደብ አገልግሎቱን ቢያዘምን ከዚህ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል የባሕር ትራንስፖርት ተጠቃሚ የአካባቢው ነዋሪዎች አመላክተዋል፡፡ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ደቅ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሃይማኖት አረጋ ለአብመድ እንደተናገሩት የድርጅቱ የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባዎች አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አይደለም፡፡ የተሟላ የወደብ አገልግሎት ባለመኖሩም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች እየተቸገሩ ነው፡፡

አብመድ በጉዳዩ ላይ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙላት ፀጋን አናግሯል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ የጀልባዎቹን ጥራትና ምቾት ለማሳደግ፣ የወደቦችን ደረጃ ከፍ ለማድረግና የመዝናኛ ቦታዎቹን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን ለዓመታት ሁለገብ አገልግሎት ስትሰጥ የነበረችውን ‹የጣና ነሽ› ጀልባ ሞተር እየተቀየረላት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ‹የካቲት› የምትባለውን ጀልባ ሞተር ለመቀየር ታቅዷል፡፡

ካሉት ወደቦች መካከል ደግሞ የዑራ ኪዳነ ምሕረትና የጅግርሳ ወደቦች እድሳት ተሠርቷል፡፡ መሐል ዘጌና ደቅ ደሴት ቆታ ማርያም አካባቢ የሚገኙ ደሴቶችን ለማልማትም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ሥራ አሥኪያጁ አብራርተዋል፡፡

በጎርጎራና ቁንዝላ ወደቦች የሚገኙ የመዝናኛ ቦታዎችን የበለጠ ለማልማትና ገቢያቸውን ለማሳደግ ከባለሀብቶች ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እንደታቀደም ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅቱ ስድስት የሚደርሱ የመዝናኛ ቦታዎችን ያስተዳድራል፤ የ10 የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ጀልባዎች እና የ10 የጀልባዎች መዳረሻ ወደቦች ባለቤትም ነው፡፡

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ከ13 ሚሊዮን 102 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here