የጥምቀት በዓልን ከሚያከብሩ ሀገራት በተለየ የኢትዮጵያ ጥምቀት ለምን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሊመዘገብ ቻለ?

0
125

ባሕር ዳር፡- ጥር 11/2012ዓ.ም (አብመድ) ጥምቀት በአብዛኞቹ የዓለማችን ሀገራት የሕዝብ ክብረ በዓል በሚል ይጠራል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከተከበረ ከ12 ቀናት በኋላም ይከበራል፡፡ ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በቅዱስ ዩሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን በማስታወስ ይከበራል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ወድቀው በመስገድና ሣጥኖቻቸውን በመክፈት እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ያቀረቡትን ሰብአ ሰገል የሚያስታውሱበትም ነው፡፡

 

ጥምቀትን መገለጥ የሚል ትርጓሜም ይሰጡታል፡፡ የሰብአ ሰገል ጉብኝትም ይሁን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ የኢየሱስን መገለጥ የሚያሳዩ አስፈላጊ ሁነቶች እና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ጊዜያት መሆናቸውን ያመላክታል፡፡

 

ጥምቀት በዋናነት በኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ይከበራል፡፡ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ጥምቀትን ሁለቱንም ማለትም የሰብአ ሰገል ጉብኝትንና የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅን በማሰብ ያከብሩታል፡፡

በስፔን ወላጆችና ልጆቻቸው በሰዎች በተጨናነቀው ጎዳና በአስደናቂና ሳቢዎቹ ትዕይንቶች ላይ በመታደም ሥነ ሥርዓቱን ይከታተላሉ፡፡ የሰብአ ሰገል ሰዎች ለህፃኑ ኢየሱስ ስጦታ ለማቅረብ ረጅም መንገድ መጓዛቸውን በማስታወስ የበዓል አከባበሩ ይካሄዳል፡፡

 

ሕጻናት ሰብአ ሰገል ተብለው ለተሰየሙ ሰዎች ስጦታ የሚጠይቁበትን ደብዳቤ ይጽፋሉ፡፡ ሰብአ ሰገል ለኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ እንዳቀረቡ ሁሉ ሕጻናት ስጦታዎችን ይቀበላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሕጻናት ጠዋት ላይ ስጦታዎችን ለማግኘት ምሽቱን ሙሉ ጫማቸውን ከቤት ውጭ ያሳድራሉ፡፡

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹‹የሽብር ጥቃቶች ሊቃጡ ይችላሉ›› በሚል ፍርሃት በማድሪድና ባርሴሎና በጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር በዓሉ ይከበራል፡፡ ትዕይንቶቹ በሚካሄዱባቸው መንገዶች ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ይታገዳሉ፡፡

በቸክ ሪፐብሊክ ርእሰ ከተማ ፕራግ የጥምቀት በዓሉን የሚያደምቁ የትዕይንተ ሕዝብ ሥነ ሥርዓቶች ይደረጋሉ፡፡ ከቻርልስ ድልድይ ዳርቻ (ጎን) በቀዝቃዛው ቪልታቫ ወንዝ የቸክ ዜጎች በመጠመቅና በመዋኘት ተሳታፊ ይናሉ፡፡

በቡልጋሪያ፣ ግሪክና ሩሲያ ገንዳ ተዘጋጅቶ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል፡፡

በአውስትራሊያ ሜልቦርን አቅራቢያ በፍራንክስቶን ውኃ ዳርቻ ዓመታዊ በውኃ የመባረክ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡

 

በሜክሲኮ ደግሞ “ሮስካ ዲ ሬየስ” ብለው የሚጠሩትን ጣፋጭ ዳቦ ያዘጋጃሉ፡፡ በዳው ውስጥ በፕላስቲክ ወይም በሸክላ በጨቅላ ሕጻን ቅርፅ የተሠራ አሻንጉሊት ይደብቃሉ፡፡ ቅዱሱ ቤተሰብ ኢየሱስን ከሄሮድስ መደበቅ እንዳስፈለገው ለማመላከት የታሰበ ነው፡፡

 

በጣሊያን በርካታ ሕጻናት በበዓሉ የዋዜማ ቀን ስጦታዎችንና ከረሜላ ለማግኘት ማልደው ይነሳሉ፡፡ “ቤፋና” የተሰኘችው አዛውንት ሴት ስጦታ ታቀርብልናለች ብለው ስለሚያምኑ ለገና ተብለው የተሠሩ የካልሲ ቅርፅ ያላቸው ዘንቢሎች ያስቀምጣሉ፡፡ የስጦታ ዕቃዎቹ እንዲሞሉበት በማሰብ የመጣ ነው፡፡

 

በቤልጂየም ሕጻናት ልክ እንደ ሰብአ ሰገል ሰዎች ለብሰው በየሰው ቤት በር ለበር እየሄዱ ይዘምራሉ፡፡ ሰዎቹም ገንዘብና ጣፋጭ ምግቦች ይሰጧቸዋል፡፡ በፖላንድም በተመሳሳይ ሕጻናት የማይጠገብ የዝማሬ ቅላፄዎቻቸውን ለማሰማት ይወጣሉ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት ልደት ከተከበረ ከ12 ቀናት በኋላ ይከበራል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ መሠረት በማድረግ ከተራ፣ ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ በሚል ስያሜ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይከበራል፡፡

ዘንድሮ ጥር 11/ 2012 ዓ.ም የሚከበረው የጥምቀት በዓል ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ለበርካታ ዓመታት ጥምቀትን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሲደረግ የነበረው ጥረት መሳካቱ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ጥምቀትን በማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ አካትቶታል፡፡

 

‹‹ጥምቀትን በኢትዮጵያ የተለየ የሚያደርጉት ሦስት ትልልቅ ጉዳዮች አሉት›› ያሉት ሰባኬ ወንጌል ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ናቸው፡፡ ታቦት ይዞ የመውረድ ሥነ ሥርዓት መኖሩ አንደኛው ነው፡፡ ‹‹አማናዊው ጉዳይ በአዲስ ኪዳን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ለማክበር ለክርስቶስ የሚሰዋበት፣ በዕለቱ ቅዳሴ የሚቀደስበትና ስጋ ወደሙ የሚፈትቱበት ነው፤ የእርሱ ማደሪያ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያኗ እርሱን ማክበሯን ለመግለጽ በዛም ያለ ታቦት ሌሊት ስለማይቀደስ ነው ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቱን የምታካሂደ›› ብለዋል ዲያቆን ብርሃኑ፡፡ በብሉይ ኪዳን ይተገበሩ የነበሩ ሥርዓቶች ከአዲስ ኪዳን ጋር ሳይቃረኑና ሳያፋልሱ ጥቅም መተግበራቸውንም አብራርተዋል፡፡

ሌሎች የዓለም ሀገራት ጥምቀትን በበዓሉ ዕለት ብቻ ያከብሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ድንኳን ተጥሎ በተለየ ሁኔታ መሰብሰብና ማደር የሚል ትርጓሜ ከተሰጠው ከተራ ጀምሮ ሄዶ በአንድ ቦታ ማደሩ ሁለተኛ ምክንያት ነው፡፡ ሦስተኛው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን በመላው ኢትዮጵያ ይደረጋሉ፡፡ የቅዱስ ያሬድ የተለየ ዜማም ልዩ ያደርገዋል፤ በሌሎቹ የታየው ለውጥ ብዙም ጉዳት ሳያደርስ ጥንታዊ ሥርዓትን ጠብቆ መቆየቱ እና ጥንታዊ የክርስትና በዓላት አከባበር ትውፊት (ገቢር) ሳይጠፋ መገኘቱ የመንግሥታቱ ድርጅት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘግበው እንዳስቻለ ሰባኬ ወንጌል ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ነግረውናል፡፡

 

ምንጭ፡- የምስልና የመረጃ ምንጭ፦ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ታይም ኤንድ ዴት፣ ዋይ ክሪስማስ

 

በኪሩቤል ተሾመ

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here