የፀጥታ ኃይሉ የበረሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አበረታች የመከላከል ተግባር እየፈፀመ መሆኑ ተገለፀ፡፡

0
18

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የበረሃ አንበጣ በምሥራቅ አማራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር፣ በደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎች ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ከባሕላዊ የመከላከያ ዘዴ እስከ ዘመናዊ የኬሚካል ርጭት ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡ በባሕላዊ መንገድ አንበጣውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ከአርሶ አደሩ ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላት ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል እያበረከቱት ያለው በጎ ተግባር ሊበረታታ እንደሚገባ የየዞኖቹ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሉ ከሕዝብ ጎን በመሆን እየተወጣ ባለው የአንበጣ መንጋ መከላከል ሥራ በሰብል ላይ ሊደርስ የነበረውን ተጨማሪ ውድመት መቀነሱን የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል አስረድተዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን ከጥቅምት 1/2012 ዓ.ም ጀምሮ የበረሃ አንበጣ እንደተከሰተ የጠቆሙት ዲያቆን ተስፋሁን ‹‹በሀብሩ፣ ጉባ ላፍቶ፣ ራያ ቆቦ ወረዳዎችና ቆቦ ከተማ አስተዳደር በባሕላዊ መንገድ እየተደረገ ያለው የመከላከል ሥራ አበረታች ውጤቶችን አሳይቷል›› ብለዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ እየቀነሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መንጋው በደቡብ ወሎ ዞን ጉዳት እያደረሰባቸው በሚገኙ ወረዳዎች የፀጥታ ኃይሉ መሰማራቱና እያሳየ በሚገኘው ባሕላዊ የመከላከል በጎ ተግባር ውጤታማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ ናቸው፡፡ ኃላፊው ሠራዊቱ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን በእንደዚህ ዓይነት የአደጋ ወቅት የሕዝብ ልጅ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኦፕሬሽን ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ጌታቸው ብርሌ አባላቱ የበረሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢ እያሳዩት ካሉት የመከላከል እገዛ በተጨማሪ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም በልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ሲሳተፉ መቆየታቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ተመሳሳይ የሰብል ስብሰባ ሥራዎች ሲከውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይም የክልሉ ልዩ ኃይልና ሌሎችም የፀጥታ ኃይል አባላት ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here