ድርቁን መንግሥት በራሱ አሠራር ሊቋቋመው እንደሚችል ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡

0
28

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ተቋማት በዕቅድ እየሠሩ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አከባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዛሬ ጥቅምት 11/2012 በጽህፈት ቤቱ ሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዝናብ እጥረት ምክንያት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ የዋግ ኽምራ ብሔረስብ አስተዳድር ወረዳዎች የምግብ ድጋፍ ማድረስ እንደተጀመረ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኝ አደመ እንደገለጹት በዋግ ኽምራ ብሔረስብ አስተዳድር በድርቁ ተጎጅ ለሆኑ በስሃላ ሰየምት፣ በዝቋላ፣ በሰቆጣ፣ በአበርገሌ እና በፃግብጂ ወረዳዎች ለሚገኙ 126 ሺህ 90 ዜጎች የምግብ ድጋፍ እየደረሰ ነው፡፡የተረጂዎች ቁጥር የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር እያደረገ የሚገኘው የሰብል ግምገማ ሲጠናቀቅ የሚታወቅ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሯ ድጋፍ የሚሹት ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

እንደችግሩ ስፋት ለ12 ወራት የሚሆን ድጋፍ እንዲደረግ እየሠሩ መሆናቸውንም ወይዘሮ እታገኝ ተናግረዋል፡፡
ድርቁን መንግሥት በራሱ አሠራር ሊቋቋመው ይችላል፤ ለዜጎቹ ድጋፍ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንም በህጋዊ እና በተቀናጀ አግባብ ማከናወን ይቻላል ብለዋል ወይዘሮ እታገኝ፡፡

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ጀምበሩ ደሴ በበኩላቸው በክልሉ ድርቅ በክልሉ ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር በተጨማሪ በሰሜን ወሎ ዞን – ራያ ቆቦ እና ሀብሩ አከባቢዎች፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን – ምስራቅ በለሳ አካባቢ በሚገኙ 4 ቀበሌዎች፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ በጃናሞራ አካባቢ 10 ቀበሌዎች ላይ መከሠቱን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ተቋማት በመቀናጀት ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድ፣ የውሃ እና የእንስሳት መኖ አቅርቦትን በተመለከተ እቅድ እንዳዘጋጁ አቶ ጀምበሩ ተናግረዋል፡፡ ዕቅዱንም የክልሉ መንግሥት አፅድቆ ወደ ሥራ እንዲያስገባ መምራታቸውን ነው በተለይም ለአብመድ የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here