ጉራጌ ሀብታም የሚሆነው በሥራ ብቻ ሳይሆን በአባቶቹ ምርቃት ነው፡፡

0
132
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2012 ዓ/ም (አብመድ) ወርኃ መስከረም ሲጋመስ፣ የአደይ አበቦች ምድርን ሲያስጌጡ፣ የመስቀል አእዋፋት ሲራወጡ፣ ተራራ እና ኮረብቶች በኅብረ ቀለማት ሲንቆጠቆጡ እና ከተራራው የሚወርደው ጅረት ባዘቶ ሲመስል ምድር የነገሥታት ካባ ትመስላለች፡፡ በመስከረም ምድር አዲስ መልክ ስትለብስ ፍጡር ሁሉ አዲስ ተስፋ ይሰንቃል፡፡ በዚህ አዲስ እና ውብ ወራት ላይ በዓላት ሲጨመሩ ደግሞ ውበቱ የበለጠ ይጎላል፡፡
 
ኢትዮጵያውያን ሥራ አቁመው መስሪያ ቤት ዘግተው ከሚያከብሯቸው በዓላት መካከል በወርኃ መስከረም አጋማሽ የሚከበረው የመስቀል በዓል አንዱ ነው፡፡ መስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም አቅጣጫ በድምቀት ይከበራል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባባር ለየት የሚልበት ድባብ አለው፡፡ አካባቢው በልምላሜ እጽዋት የተዋበ ነው፡፡ የእንሰት እና ሌሎች እፅዋቶች ለምድሯ ጌጦች ናቸው፡፡ ሰው ሥራ ወዳድ ነው፡፡ ይህ ድንቅ ማኅበረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ በርካታ ማኅበረሰቦች መካከል አንዱ ነው፤ የጉራጌ ማኅበረሰብ፡፡
ጉራጌ ሲነሳ ሥራ ወዳድነት ቅንነት፣ ተግባቢነት፣ አርቆ አሳቢነት እና ባለ ራዕይነት ይታወሳሉ፡፡ ለጉራጌ ሁሉም ሀገሩ ነው፡፡ ሁሉም ወገኑ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ድንቅ የሆነ ማኅበረሰብ የመስቀል በዓል ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል፡፡
 
የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ አለፍ ሲል ባሕላዊ ገጽታው እና አንድምታውም የተለየ ነው፡፡ አቶ ሳኅሌ አስፋው የተባሉ የጉራጌ ዞን ነዋሪ ‹‹መስቀል በጉራጌ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው፤ መስቀል በጉራጌ ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ወዳጅ ዘመዶች የሚገናኙበት፣ ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሰረዝበትና ምርቃት የሚወርድበት ነው፡፡›› አሉን፡፡
 
ከጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች የመስቀል በዓል ሲቃረብ ለቤተሰቦቻቸው፣ ልብስ፣ ጫማ፣ የመስቀል በዓል ቀን የሚታረድ በሬ የሚሆን ገንዘብ እየያዙ ወደ ቤተሰብ ይተማሉ፡፡ በጉራጌ ብሔረሰብ ሀብት እና ጸጋ የሚገኘው ከአባቶች ምርቃት እና ከእነሱ በረከት በማግኘት እንደሆነ ይታመናል፡፡ መልካም አድርጎ የተመረቀ ልጅ ሁሉ ሀብታም፣ ጤነኛ፣ ሰው የሚወደው እና መልካም እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ቀደም ሲል በጉራጌ ብሔረሰብ የመስቀል ቀን የቀረ ልጅ የሞተ እስኪመስል ድረስ ቤተዘመዱ ያዝን ነበር፡፡ በተቻለ መጠን ያልመጣው ልጅ ከእርድ በፊት እንዲመጣ ፈላጊ ይላክበት እንደነበርም አቶ ሳኅሌ ነግረውናል፡፡ አሁን ከዘመኑ ጋር መገናኛው ስለበዛ ለፍለጋ የሚላከው ሰው ቀንሷል፤ ግፋ ቢል ስልክ ደውሎ መጥራት ስለሚቻል፡፡
Related image
 
በጉራጌ ዞን የባሕልና ቱሪዝም ባለሙያው አቶ መንግሥቱ አበራ ስለበዓሉ አከባበር ሐሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የመስቀል በዓል ከመስረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ቀን ይከበራል፡፡ በጉራጌ ማኅበረሰብ ሴት ልጅ የወለዱ እና ለሚስትነት የሰጡ ወላጆች የተለየ ክብር ይሰጣቸዋል፡፡ በመስቀል ሳምንትም የስጦታ እቃ ተይዞ ይጎበኛሉ፡፡
 
የመስቀል በዓል መከበር የሚጀመረው መስከረም 12 እንደሆነም አቶ መንግሥቱ ነግረውናል፡፡ መስከረም 12 የቤት ዕቃዎች ወጥተው የሚጸዱበት፣ ቤት የሚለቀለቅበት እና አጠቃላይ በቤት ውስጥ ያሉ ቁሳቁስ ሁሉ ለበዓሉ ጽዱ የሚሆኑበት ቀን ነው፡፡ በቀን 13 ደግሞ የጉራጌ እናቶች ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉበት ነው፡፡ በቀን 14 የጎመን ክትፎ በቂቤና በአይብ የሚዘጋጅበት ቀን ነው፡፡ ይህ የጎመን ክትፎ መስከረም 15 ከሚደረገው የእርድ ሥነ-ስርዓት ቀደም ብሎ የሚካሄደው የልጆች ሆድ እንዲፍታታ እንደሆነም ይነገራል፡፡ የበዓል ምግብ በጎመን ክትፎ የጀመረ ሁሉ የእርዱ ቀን ስጋ ሲበላ እንዳይቸገር ወይም ሆዱን እንዳያመው ለማድረግ ነው፡፡ ስሙም ‹‹ዝማ መጀት›› ይባላል፡፡ መስከረም 15 የመስቀል ከብት እርድ ይከናወናል፡፡
 
እርዱ የሚጀምረው በዕድሜ ከፍ ካሉት እማወራና አባወራ ቤት ነው፡፡ ከሁሉም ቤት እርድ ስለሚኖር ሥነ-ስርዓቱ የሚቀጥለው በዕድሜ ደረጃ ይሆናል፡፡ ከብት ሲታረድ የጉራጌ አዛውንቶች የበሬውን ሻኛ ይዘው በሬውን ልጅ ገዝቶት ከሆነ ‹‹ሀብትህ(ሽ) እንደ በሬው ጸጉር የበዛ ይሁን፣ የወለዳችሁት ይባረክ፣ ገበሬው ምርቱ ይትረፍረፍ ጎተራው ይሙላ፣ የተማረው ለመልካም ነገር አዕምሮው ይከፈት፣ ሸረኛና ምቀኛን ልብ ይስጠው፣ አውሎ አሳዳሪ መንግሥት ይስጠን፣ ሀገራችን ሠላም ትሁን…›› እያሉ ሲመርቁ የተቀረው ሰው እጁን ዘርግቶ አሜን ይላል፡፡ ምርቃናቸው ሙሉ ለሙሉ እንደሚደርስም ይታመናል፡፡ ምርቃኑ በእየቤቱ ሲታረድ ይቀጥላል፡፡
በቀን 16 ደግሞ የደመራ በዓል ይከበራል፡፡ የመጀመሪያው ደመራ የሚደመረው ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም አማኙ ሁሉ ይሰበሳባል፡፡ ምርቃትም ይደረጋል፡፡ ሰውም አሜን ይላል፡፡ በዚሁ ወቅት ብር ይሰበሰብና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያናቸው ለሚሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ይሰጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ደመራ ሲጠናቅቅ የቀየው ሕዝብ ወደሚገናኝበት ሌላ ደመራ ይሄዳል፡፡ በዚያም ምርቃት አለ፡፡ በየቤቱ ወደ ተደመረው ደመራም ይኬዳል፡፡ ምርቃኑም ይቀጥላል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ዘመድ አዝማድ እየተዞረ ይጠየቃል፡፡ በመስቀል በዓል ያዘነ ይጽናናል፤ የተጣላ ይታረቃል፤ የተጣሉት ሰዎች ባይገናኙ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ሄደው ቂም እንደሻሩ ቃል ገብተው ይመለሳሉ፡፡
በቀን 17 የእርድ ዝግጅቱ በተፈጸመ በሦስተኛው ቀን ማለት ነው የሻኛ ቀን ተብሎ ይከበራል፡፡ በዚህ ቀን በየቤቱ የታረዱት በሬዎች ሻኛ ይሰበሰብ እና በዕድሜ ትልቅ ወደ ሆኑት አባቶችና እናቶች በመሄድ ባሕሉን በጠበቀ መልኩ የምግብ ዝግጅት ይኖራል፡፡ በጉራጌ ባሕል የትኛውም ልጅ ርቀት አይገድበውም፡፡ ከወላጆቹ እና ከቀየው ትልልቅ ሰዎች ምርቃት ለመቀበልና ወላጆቹን ለማስደሰት የመስቀል ሳምንት ወደ ስፍራው ይተማሉ፡፡ የእርዱ እና ሌሎች ዝግጅቶች በእነዚህ ቀናት ይጠናቀቁ እንጂ በዓሉ እስከ ጥቅምት 5 ይዘልቃል፡፡
 
ከመስቀል በዓል ጀምሮ ‹‹አዳብና›› የሚባለው የልጃ ገረዶች ጨዋታ በየገበያውና በተለያዩ አካባቢዎች ደምቆ ይሰነብታል፡፡ በዚህ በዓል ልጃገረዶች በነጻነት የሚጫወቱበት፣ እጮኛቸውን የሚመርጡበትና አዲሱን ዓመት በደስታ የሚያበስሩበት ጨዋታ ነው፡፡ ጎረምሶች ለልጃገረዶች ሎሚ፣ ብርቱካን እና ሸንኮር አገዳ እየሰጡ የሚፈልጓትን የሚመርጡበት ምርጫቸው ከተሳካም የወደ ፊት የትዳር አጋራቸውን የሚያገኙበት ጨዋታ ነው፡፡
ጉራጌ “ሰለጠን” የሚሉት የዓለም ሀገራት ስለሴቶች መብት መከበር ሕግና ሥርዓት ሳያውጁ በፊት ‹‹አንትሮሽት›› የሚባል የሴቶችና የእናቶች ቀን አላቸው፡፡ በዚህ ቀን ለእናቶች የተለየ ክብር የሚሰጥበትና መብታቸው እንዲከበር የሚደረግበት ቀን ነው፡፡ ‹‹ነቆ›› የተሰኘ የወጣት ሴቶችና የሙሽሮች ቀንም አላቸው፡፡ በዚህ ቀን ‹‹ኩርፎ›› የተባለ ባሕላዊ አጨፋፈር ሲጨፈር ልጃገረዶች ‹‹አንባሬ አንባሬ›› እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ በዓላቱ የአስተርዮ ማርያምን ክብረ በዓል ተከትለው የሚመጡ እንደሆነም አቶ መንግሥቱ ነግረውናል፡፡
 
ጉራጌዎች ‹‹ጆካ›› የሚባል ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓትም አላቸው፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ ረጅም ዘመን ተሻግሮ የመጣ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ በድብቅ የተሰሩ ወንጀሎችንና ጥፋቶችን በሚስጢር አውጣጥቶ ለእርቅ እና ለፍርድ የሚያቀርብ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ድንቅ የሆነ ባሕላዊ ሥርዓት በዓለም እንዲታወቅ የተሠራ ሥራ እንደሌለም ባለሙያው ነግረውናል፡፡
የጉራጌ ማኅበረሰብ የመስቀል አከባበር አጭር ቅኝት ቋጨን፡፡
ሠላም ለሁሉም! እንኳን አደረሳችሁ፡፡
 
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here