ጉዲያ የባሕል ቡድን መንታ መንገድ ላይ ነው፡፡

0
33

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕል ቡድን ከተለያዩ ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች በመቋቋም የአካባቢውን ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ወግ እና ባሕል በማስተዋወቅ ክፍተኛ ድርሻ እንዳለው ይታውቃል፡፡ ‹ጉዲያ› የተባለ የባሕል ቡድን በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ስር በመሆን ለስምንት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ ሲያሳይና የብሔረሰብ አስተዳደሩን ባሕል ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ የባሕል ቡድኑ 13 ቋሚ እና ተባባሪ አባላት አሉት፡፡

ባሕል ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያቀርባቸው ሥራዎች የመድረክ ፈርጥ እየሆነ በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚገኙት የባሕል ቡድኖች ሁሉ ተመራጭ እየሆነ የመጣ ነው፡፡ ጉዲያ የባሕል ቡድን በ2011 ዓ.ም በብሔረሰብ አስተዳደር ደረጃ በተካሄደው የባሕል እና ሙዚቃ ፊስቲቫል ቀዳሚ በመሆን የዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ነገር ግን ከእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ድጋፍ እና ክትትል አለመደረጉን የቡድኑ አባላት ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ በማጣታቸውም ‹‹የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተናል›› ነው ያሉት 11 የቡድኑ አባለት፡፡

ሀብታሙ ወንድም የጉዲያ የባሕል ቡድኑ መሪ ነው፡፡ ባሕል ቡድኑ ከዚህ በፊት የሚያገኛቸውን መድረኮች በመጠቀም እና ልዩ ልዩ ሥራዎችን በማቅረብ ኅብረተሰቡ ለሥራ እንዲነሳሳ እና የብሔረሰብ አስተዳደሩ ባሕል እና ቋንቋ ጎላ ብሎ እንዲተዋወቅ የአቅማቸውን እንደሠሩ ተናግሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሥራ ኃላፊዎች ለቡድን አባላት ተገቢውን ድጋፍ እና ከትትል ያለማድረጋቸው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ እንዲያስገቡ እንዳደረጋቸው አስታውቋል፡፡

‹‹ከእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ጋር መግባባት አልተፈጠረም፣ የአንድ ወር ደመወዝም አልተከፈለም፡፡ እኛ ጀማሪ ሙያተኞችን ገንዘብ ሳይሆን ፍቅር ነበር የሚገዛን፤ የሥራ መሪዎች በሥራችን ልክ ድጋፍ እና ክትትል ባለማድረጋቸው ከምንወደው ሥራ እንድንርቅ ተገድደናል›› ብለዋል የባሕል ቡድኑ አባላት፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ተስፋ የጉዲያ የባሕል ቡድን ከዓመት ዓመት የተሻሻሉ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ በማቅረብ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ወግ፣ ባሕል እና ቋንቋ በማስተዋወቅ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡ የባሕል ቡድኑ ደመወዝ እና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር መሰብሰብ እንዳለበት መመሪያ መጽደቁንም አስታውቀዋል፡፡ የባሕል ቡድኑ ከአዳራሽ እና ከመሣሪዎች ኪራይ ገቢ በመሰብሰብ የደመወዝ እና ውሎ አበል ሲከፍል መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን የባሕል ቡድኑን በአዲስ ማደራጅት ስለተፈለገ ነባሮችንና አዳዲስ ተቀጣሪዎችን በማጣመር ይዋቀራል›› ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
የቲያትር፣ የሙዚቃ እና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ተመድቦላቸው ድጋፍ እና ክትትል ሲደረግላቸው እንደቆየም ተናግረዋል፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ገረመው ታመነ ደግሞ የጉዲያ የባሕል ቡድን በተለያዩ መድረኮች በመገኘት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ ባሕሉ እንዲተዋወቅና ኅብረተሰቡ በባሕሉ እንዲኮራ ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የባሕል ቡድኑ አባላት ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ተገቢ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ባሕል ቡድኑን ለማጠናከር ከ150 ሺህ ብር በላይ መመደቡንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ተመልሰው መደበኛ ሥራ እንዲሠሩ ይደረጋል›› ሲሉም ከንቲባ ገረመው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here