ጎንደር ለወር በሚዘልቅ ጾምና ጸሎት ላይ ትገኛለች፤ ስለሀገር ሠላምና አንድነት እየማለደችም ነው፡፡

0
248

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአርባ አራቱ ታቦታት መገኛ በመሆኗ የምትታወቀው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የሁሉም ሃይማኖቶች ተከታዮች በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት ነች፡፡

ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ መዲና ሆና ያገለገለችው ታሪካዊቷ ከተማ የታሪካዊ አድባራት ምዕመኖቿና የሃይማኖት አባቶቿ በወቅታዊ የሀገሪቱ ችግሮች አሳሳቢ መሆን የተነሳ ጸሎት ላይ ናት፡፡

የከተማዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ወደ ርዕሰ አድባራት አደባባይ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ነጭ ለብሰው እየጎረፉ በጾምና ጸሎት ስለሠላም እየለመኑ ነው፡፡ ከታላቁ የጃንተከል ዋርካ እና ከአደባባይ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው ሰፊ አደባባይ ላይ ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች ጸሎተ ምሕላ እያደረጉ ነው፡፡

ሕጻናት በንጹሕ ልቦናቸው ስለሠላም ወደ ሠማዬ ሰማያት አንጋጥጠው ‹‹አቤቱ ፍቅር ስጠን፤ መጠላላትና መጨካከንን ከኛ አርቅ፤ ወደ አባቶቻችን ፍቅርም መልሰን›› እያሉ ነው፡፡ የጎንደር እናቶችም ‹‹አቤቱ የራሔልን እንባ ከእኛ አርቅ፤ ሀገራችንን ሠላም፣ ገበያውን ጥጋብ አድርግልን! ስለሰማያዊ እንጅ ምድራዊ ሕይወት የሚያስጨንቁንን ሁሉ አርቅልን›› በማለት እየተማጸኑ ነው፡፡
ወጣቶችም ከእናቶችና አባቶች ጎን ሆነው በጸሎተ ምሕላው ወደ ፈጣሪያቸው እየተማለሉ ነው፤ ‹‹አቤቱ ለሀገራችን ሠላም ስጥ፤ ለፍቅርም አስገዛን፤ የጥላቻ ቀንበርን አንሳልን፤ ታጋሽ ልቦናም አድለን›› እያሉ ዘወትር መማጸን ከጀመሩ ቀናት አልፈዋል፡፡

ዲያቆናት፣ ቀሳውስትና መነኮሳትም ስለኢትዮጵያ ሠላም በአደባባይ እየተማጸኑ ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ወደ አደባባይ ኢየሱስ ሄጄ በጸሎተ ምሕላው ተገኝቼ ነበር፤ ሁሉም ስለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሠላምና ፍቅር ወደፈጣሪያቸው እየተማጸኑ በአርምሞና በመዝሙር ሲለምኑ ተመልክቻለሁ፡፡ ወይዘሮ ፋሲካ ገብረማርያም የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከአንቀልባ ያልወረደ ልጃቸውን እንዳዘሉ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን ለመካፈል አነጋግሬያቸዋለሁ።

‹‹እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ችግር እንዲርቅ እና ሠላም እንዲወርድ እግዚአብሔርን በጋራ ሆነን እየለምን፣ እየተማጸንን ነው›› ብለውኛል፡፡ በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ችግር ሕዝቡ ሠላም አጥቶ ለሕይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ተዳርጎ እንደነበር አስታውሰው አሁን ያለው አንጻራዊ ሠላም እንዲቀጥልና የቀደመ ፍቅር እንዲመለስ ወደ አምላካቸው ተማጽኖ እንደጀመሩ ነግረውኛል፡፡
ትግስት ደርሶ እና ዳዊት አብዩ ታዳጊ ተማሪዎች ናቸው፤ በጸሎተ ምሕላው ላይ እየተሳፉ አገኘኋቸውና ስለሁኔታው ጠየኳቸው፤ ተመሳሳይ ሐሳብ ነገሩኝ፤ ‹‹የመጣብን ፈተና ያስፈራል፤ እንደ ልጅ ደስተኛ ሆነን ወደ ትምህርት ቤት እየሄድን አይደለም፤ ፍቅር መጥፋቱ አሳስቦናል፤ ለዚህ ነው ፈጣሪን በጋራ ለመማጸን የመጣነው›› ብለውኛል፡፡ በጎንደር አካባቢም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን አሰቃቂ ሁኔታ ሁሉ አምላክ በምሕረት ዓይኑ ተመልክቶ መቋ እንዲያሰጠው ጸሎት ለማድረግ ስለመገኘታቸው ነው የነገሩኝ።

ሊቀ ማዕምራን መንበሩ መሳፍንት የደብረ መንክራት ቅዱስ ቂርቆስ የድጓ መምህር ናቸው። ከጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ተካፍለው ሲመለሱ አነጋግሬያቸው ነበር። ‹‹በመላ ሀገሪቱ ሰው በሃይማኖቱ ምክንያት፣ ሰው በዘሩ እና በማንነቱ ምክንያት ጥቃት እየደረሰበት ነው፡፡ ይህን መዓት ለማራቅ ደግሞ ጸሎት ትልቅ ድርሻ አለው። ሕዝቡም ወደ ቀልቡ ተመልሶ እንዲያስብ፣ ማንም ቢሆን የእግዚአብሔርን ፍጡር እንዳይገል ለማድረግ እንዲህ በጸሎት አምላክን መለመኑ መልካም ነው›› ብለዋል።

በጎንደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ሰብሳቢ ዲያቆን ሰለሞን ዓለሙ ደግሞ ‹‹ጸሎት ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ ማግኛ ነው፤ ወደ ልቦና መመለሻ፣ ራስንም መግዣ ነው፡፡ በሀገራችን አሁን ያለውን ክፉ መንፈስ አምላክ እንዲያርቅና ፍቅርና ፀጋ እንዲያድለን ከጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሕዳር 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጸሎተ ምሕላችን እንደቀጠለ ነው›› ብለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት የጉባኤ መምህራን ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጉባኤ አስካል ካሣሁን ደግሞ ‹‹ሰዎች ንስሐ ገብተው ወደ ፈጣሪ እንዲቀርቡና ምሕረትን እንዲለምኑ፣ ጥላቻንና ክፋትን በጸሎት ልመና ለማራቅ፤ በማንኛውም ሁኔታ የሚጠየቁ የመብት ጥያቄዎችም ሆነ የሚሰጡ መልሶች ያለ ግጭት በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ለማድረግ አምላክ እንዲረዳን ጸሎተ ምሕላው እየተደረገ ነው›› ብለዋል።

ዲያቆን ሰሎሞን ዓለሙ ‹‹በጸሎት የሰው መንፈስ ከአምላኩ ጋር ይታረቃል። ከእግዚአብሔር መልስ አገኛለሁ ብሎም ያስባል። ልበ ደንዳና የሚባል ሰው ሳይቀር እንኳ በዚህ መንፈስ ይሸነፋል። አሁን ሀገራችን የገባችበት ችግር ጥቂት ሰዎች በፈጠሩት ችግር ብቻ የመጣ አይደለም፤ አብዛኞቻችን ፈቃደ እግዚአብሔርን መከተል ትተን ፈቃደ ሥጋን በመከተላችን የመጣ የድምር ኃጢያቶች ቁጣ ነው። ስለዚህ እንዲህ በጸሎት አምላክን ከለመንነው ይቅር ይለናል ብለን ስለምናምን የአዕምሮ እረፍት ይሰጠናል›› ብለዋል።
ሊቀ ጉባኤ አስካል ካሣሁን በበኩላቸው ‹‹በክርስትና ሃይማኖታችን እንደሚያዘው ሆነን፤ በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ዋጋ ከማያሰጡ ነገሮች ማለትም ሰውን ከመግደል፣ ቤትና ንብረትን ከማቃጠል እና ከሌሎች አስፀያፊ ተግባራት ርቀን ከለመነው ፈጣሪ ይቅር ስለሚለንና ፍቅርን ስለሚያድለን የጸሎተ ምሕላው ሚና ትልቅ ነው›› ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብዕ ኮሌጅ የሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ናሆም እያሱ ካለው ወቅታዊ የፀጥታና የደኅንነት ችግር አንጻር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ያለው ጸሎተ ምሕላ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ጸሎት የማኅበረሰብ ትስስርና አንድነትን የመፍጠር አቅም አለው። በተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱ ጥቃቶች ሕዝቡ በራስ መተማመን እንዳይኖረው፣ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እና ፍርሃት እንዲያድርገበት የሚያደርጉ ናቸው። ስለዚህ ለጸሎት ሰዎች ሲሰባሰቡ ከዚያ መጥፎ ስሜት ይወጡና በራስ መተማመናቸው ጨምሮ የማኅበረሰብ ትስስራቸውን ያጠናክርላቸዋል›› ብለዋል።

መምህሩ እንዳሉትም ጸሎት ማኅበራዊ መረጋጋትን ይፈጥራል፤ ሰዎች ከፖለቲካዊ ዕይታዎችም ወጣ ብለው የሃይማኖት አስተምሯቸውን ስለሚያስቡ ማኅበራዊ መረጋጋትን ይፈጥራል። ‹‹የሞራልና የግብረ ገብነት ግንባታን ከፍ በማድረግም ሰው መረበሹን እንዲተው ያግዛል። ካለው መጥፎ ስሜት በጸሎት ሰው የራሱን የሥነ ልቦና ሕመም ያክማል። ይህም ለሠላሙ የራሱን ትልቅ ሚና ይጫወታል›› ብለዋል መምህር ናሆም በሙያዊ ትንታኔቸው።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተድላ ደግሞ ‹‹እየተካሄደ ያለው ጸሎተ ምሕላ ሠላምን ከማምጣት አኳያ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ስለአብሮነት፣ ስለፍቅርና ስለመከባበር በሃይማኖት ተቋማቱ የሚሰጠው ትምህርት እየተሸረሸረ ያለውን እሴት ከመገንባት አንፃር ሚናው ጉልህ ነው›› ብለዋል። የሠላሙ ጉዳይ ከምንም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሕዝቡ መሠል አወንታዊ ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

 

ጥቅምት 7 ቀን የጀመረው ጸሎተ ምሕላ እስከ ሕዳር 7 ቀን የሚቀጥል ነው፤ ከጥቅምት 24 -30 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ የማኅበረ ሥላሴ እና የሌሎች ገዳማት አባቶች ባስተላለፉት መልዕክት መሠረት ስለሠላም ፆምና ጸሎት የታወጀበት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች በፆምና ጸሎቱ እንዲተጉም ዲያቆን ሰሎሞን ዓለሙ አሳስበዋል።
የማኅበረ ሥላሴ ገዳም ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የተማሩበትና በኑዛዜያቸው መሠረትም አካላቸው ያረፈበት ነው፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ስለታሪካዊው ገዳም ተከታታይ ዘጋቢ ፕሮግራሞችን በአማራ ቴሌቪዥን እያቀረበ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ፍጹምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here