ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭት ቀስቃሽ መገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠነቀቁ፡፡

0
44

“የውጭ ሀገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች… ትዕግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ላይ ከመጣ እርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መሆኑን በጥንቃቄ መገንዘበ ያስፈልጋል፡፡” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ነጥቦች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተከትሎ የመሥራት ሁኔታን የተመለከተው አንዱ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ግጭት ቀስቃሽ መገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ትኩረት ያደረጉትም የውጭ ሀገር ዜጋ ሆነው በሚዲያው ዘርፍ እየተሳተፉ ባሉት አካላት ላይ ነው፡፡ “የውጭ ሀገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን እዚህ ተጫውታችሁ፣ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሀገር ያላችሁ ሰዎች ትዕግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ላይ ከመጣ እርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መሆኑን በጥንቃቄ መገንዘበ ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ባለፊት ዓመታት ነጻ የመሆን ፍላጎትና ጥያቄ ከሚዲያ ሲቀርብ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ዐብይ፣ ሚዲያ የዘር፣ የሀይማኖት፣ የብር ነጋዴዎች መቀለጃ በመሆኑ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በሚዲያ የኢትዮጵያን ሰላም እና ዴሞክራሲ የሚያረጋግጥ ሳይሆን አንድን አካባቢ ወክያለሁ በማለት የሚደረገው ሥራ ችግር እየፈጠረ መሆኑንም ነው ለምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት፡፡

በመሆኑም የብሮድካስት ባለስልጣን የሚዲያ ነጻነትን ሳያደናቅፍ ህግ የማስከበር ሥራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ጥሩ እና ሚዛናዊ ከሆኑ ጋር ብቻ በመሆን፣ ውሸታሞችን እና የጥፋት መረጃ የሚያሰራጩትን ባለመመልከት በራሳቸው ጊዜ እንዲጠፉ ማድረግ እንዳለበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠየቁት፡፡

ዘጋቢ:- በአስማማው በቀለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here