ፋሲል ከነማ የነበሩ የተጫዋቾቹን ጥቅማጥቅሞች በማስቀጠል ለተሻለ ውጤት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

0
26

ባሕር ዳር፡ መስከረም 30/2012 ዓ/ም (አብመድ) ፋሲል ከነማ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በ2012 የውድድር ዘመን የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት እና ጨዋታ ለማሳየት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የእግር ኳስ ቡድኑ በ2011 ዓ.ም የውድድር ዘመን በነበረው ስፖርታዊ ጨዋነት የሠላም አምባሳደር በመሆን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምሥጋና ቀርቦለታል።

ምንም እንኳን በጠባብ ልዩነት ዋንጫ ማንሳት ባይችልም ለቀጣይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አርዓያ የሚያደርገውን ተስፋ ሰጪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለፈው ዓመት አሳይቷል። የቡድኑ ደጋፊዎችም በሜዳቸው ምንም ዓይነት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እንዳይከሰት የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው ተመላቷል። ይህም አስተዋይ እና ስፖርቱን በትክክል የተረዱ ደጋፊዎች እንዲባሉ ማስቻሉን የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ምክትል ፕሬዝዳንትና የጎንደር ከተማ አስተዳደር የባሕል ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊው አቶ አስቻለው ወርቁ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ችግር የፈጠሩ ቡድኖች ቢኖሩም የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ የጎንደር ከተማ ስፖርት አፍቃሪ ሕዝብ እና የቡድኑ መሪዎች ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር የእነዚያን ቡድኖች መሪዎች፣ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች በሠላም ተቀብለው በእውነተኛ የእንግዳ አክባሪነት መንፈስ ተንከባክበው በሠላም እንዲመለሱ ማድረጉን ነው አቶ አስቻለው ያስታወሱት።

ይህን ስፖርታዊ ጨዋነት በዘንድሮው የውድድር ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ፋሲል ከነማ ያስታወቀው። ስፖርታዊ ጨዋነቱ ውጤታማ እንዲሆን ግን ባለፈው ዓመት ችግር የነበረባቸው ቡድኖች ራሳቸውን አስተካክለው መቅረብ እንደሚገባቸው አቶ አስቻለው አሳስበዋል። በተሻለ የጨዋታ ብቃት እና በጥሩ የውድድር መንፈስ በመጫወት በውድድር ዓመቱ ዋንጫ ለማንሳት ማቀዳቸውን አቶ አስቻለው አስታውቀዋል። ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ 25 ሚሊዮን ብር እንደመደበ ነው የገለጹት።
የነባር ተጨዋቾችን ውል በማደስ እና አዳዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም ስብስቡን ያጠናከሩ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ‹‹አስተዳደር ክፍሉ፣ አሰልጣኙና ተጨዋቾች ጥሩ መስተጋብር ፈጥረው እየሠሩ ይገኛሉ። አሁን ላይም በባሕር ዳር ከተማ ልምምዳቸውን እየሠሩ ነው የሚገኙት›› ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የነበረው የተጨዋቾች የደመወዝ ክፍያ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም ባሉበት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከመደበው ገንዘብ በተጨማሪም በደጋፊዎች ማኅበሩ አማካይነት ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን እንደሚጠቀም አስገንዝበዋል።

በተያያዘ ዜና ፋሲል ከነማ ስፖርት ቡድን የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን እና የታዳጊዎችን አደረጃጀት ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳቱ አስታውቀዋል። ስፖርት ቡድኑ ቀደም ብሎ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን አቋቁሟል። ባለፈው ዓመትም በፕሪሚዬር ሊግ እየተሳተፈ መቆየቱን ከቡድኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፤ ተተከ ቡድንም አለው። ይሁን እንጂ የሴቶች እግር ኳስ ቡድኑን እና የተተኪዎችን አደረጃጀት በተገቢው መንገድ የተዋቀረ ነው ለማለት አያስደፍርም። ይንንም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለማስተካከል መታቀዱን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ፎቶ፡- ከፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ገጽ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here