0
33

“አማራ ክልልን የቱሪዝም መለያ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡” የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ

ባሕር ዳር ጥር 9/2012ዓ.ም (አብመድ) ክልሉ በቱሪዝም ሀብቱ መለያ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ባህልና ቱሪዝም ቢሮው አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል በታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች የታደለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መዳረሻዎችን በተፈለገው ደረጃ ሳይጠቀምባቸው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የቱሪዝም ሀብቶችን በመለየት እና ቅድመ ተከተል በማስያዝ መዳረሻዎቹን የክልሉ መለያ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን አዳነ (ዶክተር) በተለይ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡ በዚህም አማራ ክልል የቱሪዝም መለያ እንዲያገኝ በማስቻል ባለው ሀብት ልክ እንዲጠቀም ለማድረግ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡

ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ እንዲታወቅ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ እየሠራቸው ከነበሩ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የጥምቀትን በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ ማድረግ እንደነበረም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የልደት በዓል በላል ይበላ (ቤዛኩሉ) እንዲመዘገብ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ነው ዶክተር ሙሉቀን የተናገሩት፡፡

የአዊ የፈረሰኞች ጉግስም ራሱን ችሎ ልዩ ሆኖ እንዲታወቅ እየተሠራ እንደሆነና ጥር 23/2012 ዓ.ም ላይም በብሔረሰብ አስተዳድሩ ልዩ የፈረሰኞች ቀን እንደሚከበር አስረድተዋል፡፡
ታሪካዊውን የሾንኬ የሰፈራ መንደርን ለመጠገን፣ ጥንታዊ የፈራረሱ መስጅዶችን ለማደስ እና የአካባቢው ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ዶክተር ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ከኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም በደሴ ከተማ እና አካባቢው መንዙማንና የሙስሊም ታሪካዊ አስተምህሮዎችን አጉልቶ ለማውጣት ሥራ እንደተጀመረ ነው የገለጹት፡፡ እንደ ቢሮ ኃላፊው መረጃ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here