5ኛው ወርኃዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በባሕር ዳር ተካሂዷል፤ ለከተማዋ ጽዳትም አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡

0
92

ባሕር ዳር ጥር 1/2012 ዓ.ም የተለያዩ የአካል ብቃት ማኅበራትን፣ የስፖርት ማዕከላትን እንዲሁም አጋር አካላትን ያሳተፈ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተካሂዷል፡፡ ሰፖርታዊ እንቅስቃሴው የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በአገልግል በጎ አድራጎት ድርጅት አዘጋጅነት 5ኛው ወርኃዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው ዛሬ በባሕር ዳር የተካሄደው፡፡ ወሩ በገባ የመጀመሪያው እሑድ የሚካሄደው ይህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሁሉንም የከተማውን ማኅበረስብ፣ የስፖርት ማዕከላትንና ሲቪክ ማኅበራትን ያሳተፈ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ጤናን ለመጠበቅና ከተማዋን ጽዱ ለማድርግ ዓላማ ያደረገ መሆኑንም የአገልግል በጎ አድራጎት ማኅበር አስውቋል፡፡

ማኅበሩ አንዳስታወቀው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማኅበረስቡ ዘንድ ጤናን ለመጠበቅ አስፈላጊ ቢሆንም ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠር ከተለያዩ የአካል ብቃትና የስፖርት ማዕከላት እንዲሁም ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ነው ማኅበሩ ያስታወቀው፡፡ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ በዘለለ ውብ ጽዱና ማራኪ የሆነች ከተማ ለመፍጠርም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዝግጅቱ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዘላለም ጌታሁን ከጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ጋር በመሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴውን ለማስተባበር በቦታው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ዘላለም ገለጻ ጽሕፈት ቤታቸው በየውሩ በሚካሄደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ተሳተፊ ነው፤ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆንም የከተማ ጽዳት እየተሠራ ነው፡፡

የአካል ብቃት ተሳታፊ የነበሩ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ ‹‹ስፖርት መሥራት ጤናን ከመጠበቅ በዘለለ ጥሩ አካባቢን መፈጠር ያስችላል›› ብለዋል፡፡ የጋራ ስፖርቱ ከሕጻን እስከ አረጋውያን ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆንም አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አበባው እማኛው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here